ቅዱሳት መጻህፍት
ሞሮኒ ፯


ምዕራፍ ፯

በጌታ እረፍት እንዲገቡ ሰዎች ተጋብዘዋል—በእውነተኛ ፍላጎት ፀልዩ—የክርስቶስ መንፈስ ሰዎች መጥፎውን ከጥሩ ለይተው እንዲያውቁ ያስችላቸዋል—ሰይጣን ሰዎች ክርስቶስን እንዲክዱ እናም መጥፎ እንዲሰሩ ይገፋፋቸዋል—ነቢያት ስለክርስቶስ መምጣት ተናግረዋል—በእምነት፣ ድንቅ ነገር ይሰራል፣ እናም መላዕክቶችም ያገለግላሉ—ሰዎች ዘለዓለማዊ ህይወትን ተስፋ ማድረግ እናም ከልግስናም ጋር ፅኑ መሆን አለባቸው። ፬፻፩–፬፻፳፩ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንግዲህ እኔ ሞሮኒ፣ አባቴ ሞርሞን ስለእምነት፤ ተስፋ እና ልግስና ከተናገራቸው ቃላት ጥቂቱን እፅፋለሁ፤ ለማምለኪያ በሰሩት ቦታም በምኩራብ ባስተማራቸው ጊዜ ለህዝቡ በዚህ አይነት ተናግሮአልና።

እናም እንግዲህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እኔ ሞርሞን እናገራችኋለሁ፤ እናም በእግዚአብሔር አብ ፀጋ እናም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናም በቅዱሱ ፈቃዱ፣ በተጠራሁበትም ሥጦታ ምክንያት በዚህ ጊዜ እንድናገራችሁ ተፈቅዶልኛል።

ስለዚህ፣ የቤተክርስቲያኗ አባላት ለሆናችሁ፤ ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታይ ለሆናችሁ እናም ከዚህን ጊዜ ጀምሮ በሰማይ ከእርሱ ጋር ታርፉ ዘንድ፣ በጌታ በእረፍቱም ለመግባት እንድትችሉ በቂ ተስፋ ላገኛችሁ ይህን እናገራችኋለሁ።

እናም እንግዲህ ወንድሞቼ፤ ከሰዎች ልጆች ጋር ባላችሁ ሰላማዊ ሂደት ምክንያት ስለእናንተ እንደዚህ እፈርዳለሁ።

በሥራዎቻቸው ታውቁአቸዋላችሁ የሚለውንም የእግዚአብሔር ቃል አስታውሳለሁ፤ ሥራዎቻቸው መልካም ከሆኑ እነርሱም ደግሞ መልካም ናቸውና።

እነሆም፣ እግዚአብሔርም ክፉ የሆነ ሰው መልካም የሆነን ለመስራት አይቻለውም ብሏል፤ እርሱም ስጦታን ቢያቀርብ እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር ቢፀልይ ከእውነተኛ ፍላጎት ካልሆነ በቀር ምንም አይጠቅመውም።

እነሆም፣ ለእርሱም እንደፅድቅ አይቆጠርለትም።

እነሆም፣ ክፉ የሆነ ሰው ስጦታ የሚሰጥ ከሆነ፣ በመሰሰት ያደርጋል፤ ስለዚህ ስጦታውን ለራሱ እንዳስቀረውም አይነት ይቆጠርለታል፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ፊት እንደክፉ ይቆጠራል።

እናም በተመሳሳይ ደግሞ ሰው በእውነት ከልቡ በመፈለግ ካልፀለየ በመጥፎ ይቆጠርለታል፤ አዎን፣ እናም ለእርሱ ምንም አይጠቅመውም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንደዚህ አይነቱን ማንም አይቀበልምና።

ስለዚህ፣ መጥፎ የሆነ ሰው መልካም የሆነውን ለመስራት አይቻለውምና፤ መልካም ስጦታም አይሰጥም።

፲፩ እነሆም፣ መራራ ምንጭ መልካም ውኃን ሊያፈልቅ አይቻለውም፤ ወይም መልካም ምንጭም መራራን ውሃ ሊያፈልቅ አይቻለውም፤ ስለዚህ፣ የዲያብሎስ አገልጋይ የሆነ ሰውም ክርስቶስን ለመከተል አይችልም፤ እናም ክርስቶስን የሚከተል ከሆነ የዲያብሎስ አገልጋይ ሊሆን አይችልም።

፲፪ ስለዚህ፣ መልካም የሆኑ ነገሮች በሙሉ ከእግዚአብሔር ይመጣሉ፤ እናም መጥፎ የሆኑም ከዲያብሎስ ይመጣሉ፤ ዲያብሎስ የእግዚአብሔር ጠላት በመሆኑ፣ ያለማቋረጥ ከእርሱ ጋር ይዋጋል፣ እናም ሰዎች ኃጢያት እንዲሰሩ እናም ያለማቋረጥ ክፉ የሆኑትን እንዲሰሩ ይጋብዛቸዋል፣ እንዲሁም ይገፋፋቸዋል።

፲፫ ነገር ግን እነሆ፣ የእግዚአብሔር የሆነ ያለማቋረጥ መልካምን እንዲሰሩ ይጋብዛል እናም ይገፋፋል፤ ስለዚህ፣ መልካምን ለመስራት፣ እናም እግዚአብሔርን እንድናፈቅር እናም እንድናገለግለው የሚጋብዝ እናም የሚገፋፋ ማንኛውም ነገር ከእግዚአብሔር የሆነ ነው።

፲፬ ስለዚህ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ አድምጡ፣ ክፉ የሆነው ከእግዚአብሔር ነው በማለት፣ ወይንም መልካምና ከእግዚአብሔር የሆነውን ከዲያብሎስ ነው በማለት አትፍረዱ።

፲፭ እነሆም፣ ወንድሞቼ፣ ጥሩውን ከመጥፎ ለይታችሁ ታውቁ ዘንድ እንድትፈርዱ ተሰጥቷችኋል፤ እናም ፍፁም በሆነ ዕውቀት ልታውቁ እንድትችሉ፣ ጥሩውን ከመጥፎ የመፍረጃ መንገድ ጨለማን ከብርሃን ለይቶ እንደሚያሳይ ያህል ግልፅ ነው።

፲፮ እነሆም፣ እያንዳንዱ ሰው መልካሙን ከመጥፎው ለይቶ ያውቅ ዘንድ የክርስቶስ መንፈስ ተሰጥቶታል፤ ስለዚህ፣ እንዴት እንደምትፈርዱም መንገዱን አሳያችኋለሁ፤ መልካም ነገሮችን ለማድረግ የሚጋብዝ እናም በክርስቶስ ሰዎች እንዲያምኑ ለማሳመን የሚያደርግ የተላከው በክርስቶስ ኃይል እና ስጦታ አማካኝነት ነው፤ ስለዚህ ይህ ከእግዚአብሔር መሆኑን ፍፁም በሆነ ዕውቀት ታውቃላችሁ።

፲፯ ነገር ግን ሰዎች መጥፎ እንዲሰሩ፤ እናም በክርስቶስ እንዳያምኑ፣ እናም እንዲክዱት፣ እናም እግዚአብሔርን እንዳያገለግሉ የሚያሳምናቸው፣ ይህም ከዲያብሎስ መሆኑን ፍፁም በሆነ ዕውቀት ልታውቁ ትችላላችሁ፤ ምክንያቱም በዚህ ሁኔታ ዲያብሎስ ይሰራልና፣ እርሱም ማንንም ሰው መልካም እንዲሰራ አይገፋፋም፣ አንድም አይገፋፋም፤ መላዕክቶቹም ቢሆኑ ይህንን አያደርጉም፤ እራሳቸውን የእርሱ ያደረጉትም ቢሆኑ እንዲህ አያደርጉም።

፲፰ እናም እንግዲህ፣ ወንድሞቼ፣ በእርግጥ የምትፈርዱበትን ብርሃን ማወቃችሁን በመመልከት፣ ብርሃኑም የክርስቶስ ብርሃን ነው፣ በስህተት እንደማትፈርዱ እርግጠኞች ሁኑ፤ ምክንያቱም በምትፈርዱበት ፍርድ ደግሞ ይፈረድባችኋልና።

፲፱ ስለዚህ፣ ወንድሞቼ በክርስቶስ ብርሃን መልካሙን ከመጥፎው ታውቁ ዘንድ በትጋት እንድትፈልጉ እለምናችኋለሁ፤ እናም መልካም የሆኑትን ሁሉ የምትይዙ ከሆነ፣ እናም ካልኮነናችሁት፣ በእርግጥ እናንተ የክርስቶስ ልጆች ትሆናላችሁ።

እናም አሁን፣ ወንድሞቼ፣ እንዴትስ መልካም የሆኑትን ሁሉ ለመያዝ ይቻላችኋል?

፳፩ እናም አሁን እናገራለሁ ስላልኩት እምነት በተመለከተ እናገራለሁ፤ እናም መልካም የሆኑትን ነገሮች የምትይዙበትን መንገዱን እነግራችኋለሁ።

፳፪ እነሆም፣ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በማወቁ፣ እነሆ፣ እርሱም የሰው ልጆችን እንዲያገለግሉ፣ የክርስቶስን መምጣት በተመለከተ እንዲገልጡ መላዕክትን ልኳል፤ እናም በክርስቶስ መልካም ነገር በሙሉ ይመጣል።

፳፫ እናም እግዚአብሔር ደግሞ በአንደበቱ ለነቢያት ክርስቶስ እንደሚመጣ ተናግሯቸዋል።

፳፬ እናም እነሆ፣ መልካም ነገሮችን ለሰው ልጆች የገለጠበት የተለያዩ መንገዶች ነበሩት፤ እናም መልካም የሆኑ ነገሮች በሙሉ የሚመጡት ከክርስቶስ ነው፤ አለበለዚያ ሰዎች የወደቁ ናቸው፣ እናም መልካም ነገርም ወደ እነርሱ ሊመጣ አይቻለውም።

፳፭ ስለዚህ፣ በመላዕክት አገልግሎት አማካይነት እናም ከእግዚአብሔርም አንደበት በሚወጡት በእያንዳንዱ ቃላት፣ ሰዎች በክርስቶስ ታማኝ መሆን ጀምረዋል፤ እናም በእምነታቸውም መልካም የሆኑትን ነገሮች በሙሉ ለማግኘት ችለዋል፤ እናም ይህም የሚሆነው ክርስቶስ እስከሚመጣ ድረስ ነው።

፳፮ እናም እርሱም ከመጣ በኋላ ሰዎች ደግሞ በስሙ በማመናቸው ድነዋል፤ እናም በእምነታቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆነዋል። እናም ክርስቶስ በእርግጥም ህያው እንደሆነ ለአባቶቻችን እነዚህን ቃላት እንዲህ ሲል ተናግሯል፥ በስሜ ትክክል የሆነውን ማንኛውንም ነገር በእምነት እናገኛለን በማለት አብን ከጠየቃችሁት፤ እነሆ ለእናንተ ይሰጣችኋል።

፳፯ ስለሆነም፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ክርስቶስ ወደ ሰማይ በማረጉ እናም አብን በሰዎች ልጆች ላይ ያለውን ምህረት ለመጠየቅ በእግዚአብሔር ቀኝ እጅ በኩል በመቀመጡ ተአምራት ቆመዋልን?

፳፰ እርሱም የህጉን ፍፃሜ አሟልቶታል፣ እናም በእርሱ እምነት ያላቸውን በሙሉ የእርሱ አድርጓል፤ እናም በእርሱ እምነት ያላቸው መልካሙን ነገር በሙሉ ይይዛሉ፤ ስለሆነም እርሱም ለሰው ልጆች ጉዳይ ጠበቃ ይሆናል፤ እናም ለዘለዓለም በሰማያት ይኖራል።

፳፱ እናም ይህንን በማድረጉ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ተአምራት ቆመዋልን? እነሆ አልቆሙም እላችኋለሁ፤ መላዕክቶችም ቢሆኑ የሰው ልጆችን ማገልገላቸውን አላቆሙም።

እነሆም፣ እነርሱም በትእዛዙ ቃል መሰረት ለማገልገል፤ ጠንካራ እምነት እና በመለኮታዊነት አስተያየት በሙሉ ፅኑ አዕምሮ ላላቸው እራሳቸውን ለማሳየት ለእርሱ የተገዙ ናቸው።

፴፩ እናም በአገልግሎታቸውም ኃላፊነታቸው ሰዎችን ወደ ንሰሃ መጥራት፣ እናም አብም ለሰው ልጆች የገባውን የቃል ኪዳን ስራ ለማከናወን እና ለመፈፀም፣ በጌታ ለተመረጡት አገልጋዮችም ምስክርነታቸውን ይሰጡ ዘንድ የክርስቶስን ቃል ለመናገር በሰው ልጆች መካከል መንገዱን ለማዘጋጀት ነው።

፴፪ እናም ይህንን በማድረግ፣ የተቀሩት ሰዎች በክርስቶስ እምነት እንዲኖራቸው፣ ባለው ሀይል መሰረትም መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ስፍራ እንዲነኖረው ጌታ አምላክ መንገዱን ያዘጋጃል፤ እናም በዚህም ስርዓት አብ ለሰው ልጆች የገባውን ቃል ኪዳን ይፈፅማል።

፴፫ እናም ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፥ በእኔ እምነት ካላችሁ እኔ አስፈላጊ የሆነውን ማንኛውንም ነገር ለመስራት ኃይል ይኖራችኋል።

፴፬ እናም እንዲህ ብሏል፥ እስከ ምድር ዳርቻ ያላችሁ ሁሉ ንሰሃ ግቡ፣ እናም ወደ እኔ ኑ፣ እናም በስሜ ተጠመቁ፣ እናም ትድኑም ዘንድ በእኔ እምነት ይኑራችሁ።

፴፭ እናም እንግዲህ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ሁኔታው እንዲህ ከሆነ የተናገርኳችሁ እነዚህ ነገሮች እውነት ከሆኑ፣ እናም እውነት መሆናቸውንም እግዚአብሔር በኃይል እናም በታላቅ ክብር በመጨረሻው ቀን ካሳያችሁ፣ እናም እውነት ከሆኑስ የተአምራቱ ቀን ቆሟልን?

፴፮ መላዕክትስ ለሰው ልጆች መታየታቸውን አቁመዋልን? ወይስ እግዚአብሔርስ የመንፈስ ቅዱስን ኃይሉን ከእነርሱ አርቋልን? ወይንስ እስከመጨረሻው፣ ወይንም መሬት እስካለች፣ ወይም በምድር ላይ ለመዳን አንድ ሰው እስካለ ድረስ ይህን ያደርጋልን?

፴፯ እነሆ አያስቀርም እላችኋለሁ፤ ምክንያቱም ተአምራት የሚከናወኑት በእምነት ነው፤ እናም መላዕክቶችም ለሰዎች የሚታዩት እና የሚያገለግሉት በእምነት ነው፤ ስለሆነም፣ እነዚህ ነገሮች ካቆሙ ለሰው ልጆች ወዮላቸው፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች የሚቆሙት ባለማመናቸው ነው፣ እናም ሁሉም ከንቱ ይሆናል።

፴፰ እንደ ክርስቶስ ቃል በእርሱ እምነት ከሌላቸው ማንም ሰው ለመዳን አይችልም፤ ስለሆነም፣ እነዚህ ነገሮች ከቆሙ፣ እምነትም ደግሞ ይቆማል፤ እናም የሰዎች ሁኔታ አሰቃቂ ይሆናል፣ ምክንያቱም ቤዛነት እንዳልተፈፀመ ሆነው ይቆያሉና።

፴፱ ነገር ግን እነሆ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፤ ስለእናንተ የተሻሉትን ነገሮች እፈርዳለሁ፤ ምክንያቱም እናንተ የዋህ በመሆናችሁ በክርስቶስ እምነት እንዳላችሁ እፈርዳለሁ፤ ምክንያቱም በእርሱ እምነት ከሌላችሁ ከቤተክርስቲያኑ ሰዎች ጋር ለመቆጠር ብቁ አትሆኑምና።

እናም የተወደዳችሁ ወንድሞቼ በድጋሚ ተስፋን በተመለከተ እናገራችኋለሁ። ተስፋ ከሌላችሁ እምነትን እንዴት ለማግኘት ይቻላችኋል?

፵፩ እናም ተስፋ የምታደርጉበት ምንድነው? እነሆ በክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ እናም በትንሳኤው ኃይል ለዘለዓለም ህይወት እንዲኖራችሁ ተስፋ ይኑራችሁ እላችኋለሁ፤ እናም ይህም በእርሱ ባላችሁ እምነት ለእናንተ በገባላችሁ ቃል ኪዳን መሰረት ነው።

፵፪ ስለሆነም፣ አንድ ሰው እምነት ካለው ተስፋ ሊኖረው ይገባል፤ ያለ እምነት ምንም ዓይነት ተስፋ ሊኖር አይችልምና።

፵፫ እናም በድጋሚ፣ እነሆ እንዲህ እላችኋለሁ፣ የዋህ እና በልቡ የሚራራ ካልሆነ በስተቀር እምነት እና ተስፋ ሊኖረው አይችልም።

፵፬ ከሆነ ግን እምነቱ እና ተስፋው ከንቱ ነው፤ ምክንያቱም በልቡ የሚራራ እናም የዋህ ካልሆነ በጌታ ፊት ተቀባይነት አይኖረውምና፤ እናም ሰው የዋህ እናም በልቡ የሚራራ፣ እናም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ከሆነ እርሱ ልግስና ሊኖረው ይገባዋል፤ ልግስና ግን ከሌለው እርሱ ከንቱ ነውና፤ ስለሆነም ልግስና ሊኖረው ይገባል።

፵፭ እናም ልግስና ትታገሳለች፣ እናም ደግ ናት፣ እናም አትቀናም፣ እናም በኩራት አትወጠርም፣ የራሷን አትፈልግም፤ በቀላሉ አትቆጣም፣ ክፉ አታስብም፣ እናም በመጥፎ ስራ አትደሰትም፣ ነገር ግን በእውነት ትደሰታለች፣ ሁሉንም ነገሮች ትታገሳለች፣ በሁሉም ነገሮች ታምናለች ሁሉንም ነገሮች ተስፋ ታደርጋለች፣ በሁሉም ነገሮች ትፀናለች።

፵፮ ስለዚህም፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ልግስና ከሌላችሁ ከንቱዎች ናችሁ፣ ልግስና አትወድቅምና። ስለሆነም ከሁሉም በላይ ታላቅ የሆነችውን ልግስናን ያዙ፤ ሁሉም ነገሮች መውደቅ አለባቸውና—

፵፯ ነገር ግን ልግስና ንፁህ የክርስቶስ ፍቅር ናት፣ እናም እስከዘለዓለም ትፀናለች፤ እናም በመጨረሻው ቀንም እርሷን የያዘ መልካም ይሆንለታል።

፵፰ ስለሆነም የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ በልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ሁሉ ላይ በሚያፈሰው በዚህ ፍቅር ትሞሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔር ልጆች ትሆኑ ዘንድ፣ እርሱ እንደሆነ እናየዋለንና፣ እርሱ በሚመጣበትም ጊዜ እንደ እርሱ እንሆን ዘንድ፣ ይህም ተስፋ ይኖረን ዘንድ፣ ልክ እርሱ ንጹህ እንደሆነ እኛም ንጹህ እንሆን ዘንድ በኃይል በሙሉ ልባችሁ ሀይል ወደ አብ ፀልዩ። አሜን።