ቅዱሳት መጻህፍት
ጄረም ፩


መፅሐፈ ጄረም

ምዕራፍ ፩

ኔፋውያን የሙሴን ህግ ጠበቁ፣ የክርስቶስንም መምጣት ጠበቁ፣ እናም በምድሪቱ ላይ በለፀጉ—ብዙ ነቢያት ሕዝቡን በእውነት ጎዳና ለመጠበቅ ጣሩ። ከ፫፻፺፱–፫፻፷፩ ም.ዓ. ገደማ።

አሁን እነሆ፣ እኔ ጄረም፣ በአባቴ፣ ኢኖስ ትዕዛዝ መሰረት የእኛ የትውልድ ሐረግ ይጠበቅ ዘንድ ጥቂት ቃላት እፅፋለሁ።

እናም እነዚህ ሰሌዳዎች ትንሽ ቦታ ያላቸው በመሆኑ፣ እና እነዚህ ነገሮች የሚፃፉት ለወንድሞቻችን ላማናውያን ጥቅም ስለሆነ፣ በመሆኑም ጥቂት መፃፌ አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን የእኔን ትንቢትም ሆነ ራዕይ አልፅፍም። አባቶቼ ከጻፉትስ የበለጠ ምን መፃፍ ይቻለኛል? እነርሱ የደህንነትን ዕቅድ አልገለጹምን? እኔ እላችኋለሁ፣ አዎን፣ እናም ይህ ለእኔ ብቁ ነው።

እነሆ፣ በልባቸው ጠጣርነትና፣ በጆሮአቸው መደንቆር፣ እናም በአዕምሮአቸው መታወርና፣ በአንገተ ደንዳናነታቸው ምክንያት፤ በዚህ ህዝብ መካከል ብዙ መስራቱ አስፈላጊ ነው፤ ይሁን እንጂ፣ እግዚአብሔር ለእነርሱ እጅግ መሀሪ ነው፣ እናም እስከአሁንም ከምድረ ገፅ አላጠፋቸውም

እናም ብዙ ራዕይ ያላቸው ብዙዎች በመካከላችን አሉ፤ ምክንያቱም ሁሉም አንገተ ደንዳና አይደሉምና። እናም አንገተ ደንዳና ያልሆኑና እምነት ያላቸው ሁሉ፤ እንደ እምነታቸው፣ ለሰው ልጆች ነገሮችን ከሚገልፀው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ህብረት አላቸው።

እናም አሁን፣ እነሆ፣ ሁለት መቶ ዓመታት አለፉ፣ የኔፊ ህዝቦች በምድሪቷ ላይ በረቱም። የሙሴን ህግና የሰንበትን ቀን ለጌታ ቅዱስ አድርገው በመጠበቅ አስተዋሉ። ኃይማኖትንም አላረከሱም፤ ወይም አይሳደቡም። እናም የምድሪቷን ህጎች እጅግ የጠበቁ ነበሩ።

እናም እነርሱና፣ ላማናውያን ደግሞ በምድሪቱ ገፅ ላይ በብዛት ተበታትነው ነበር። እናም ከኔፋውያን ይበልጥ እጅግ ብዙ ነበሩ፤ እናም መግደል ይወዱ ነበርና፣ የዓራዊትን ደም ይጠጡ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ፣ ከእኛ ከኔፋውያን ጋር ለመዋጋት ብዙ ጊዜ መጥተው ነበር። ነገር ግን ነገሥታቶቻችንና መሪዎቻችን በጌታ እምነት ኃያል ሰዎች ነበሩ፤ እናም ህዝቡን የጌታን መንገድ አስተማሩ፤ ስለሆነም፣ እኛ ላማናውያንን ተቋቋምን፣ እንዲሁም ከምድራችን አስወገድናቸው፣ እናም ለከተሞቻችን ወይም የውርሳችን ቦታ የሆነውን ማንኛውንም መከላከያ መስራት ጀመርን።

እናም እጅግ ተባዛንና፣ በምድሪቱ ገፅ ላይ ተሠራጨን፣ እናም በወርቅና በብር እንዲሁም በከበሩ ነገሮችና፣ በመልካም የእንጨት ጥበብም፣ በመገንባትም፣ በማሽኖችም፣ እንዲሁም ደግሞ በብረትና መዳብ፣ እንዲሁም በነሀስ ምድሩን ለማረስ የሚያስችሉ መሳሪያዎችን እንዲሁም የጦር መሳሪያዎች በመስራት፣ አዎን ሹል ጫፍ ያለው ቀስትና፣ ሰይፍ፣ ጦር እናም ለጦርነት ሁሉንም አይነት ዝግጅት በማድረግ እጅግ ሀብታም ሆንን።

እናም ላማናውያንን ለመገናኘት እንደዚህ እየተዘጋጀን እያለን፣ እነርሱ በእኛ ላይ ሊያይሉብን አልቻሉም። ነገር ግን ለአባቶቻችን እንዲህ በማለት የተናገረው የጌታ ቃል ተረጋግጦ ነበር፥እናንተ የእኔን ትዕዛዛት እስከጠበቃችሁ ድረስ በምድሪቱ ላይ ትበለፅጋላችሁ።

እናም እንዲህ ሆነ የጌታ ነቢያት በእግዚአብሔር ቃል መሰረት እነርሱ ትዕዛዛትን ካልጠበቁ፣ ነገር ግን ወደ መተላለፍ ከወደቁ፣ ከምድር ፊት መጥፋት እንዳለባቸው የኔፊን ህዝብ አስፈራርተው ነበር።

፲፩ ስለሆነም በነቢያትና፣ ካህናትና፣ መምህራን ህዝቦችን የሙሴን ህግጋትና የተሰጠበትን አላማ በማስተማር፣ ወደመሲህ ወደፊት እንዲመለከቱና እርሱ እንደመጣም አይነት እንደሚመጣ እንዲያምኑ በትእግስት አጥብቀው በመምከር በትጋት አገለገሉ። እናም በዚህ ሁኔታ አስተምረዋቸው ነበር።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ ይህን በማድረግ ከምድር ፊት እንዳይጠፉ ጠበቋቸው፤ ልባቸውንም በቃላት ወቀሱት፣ በማከታተልም ለንስሀ አነሳሷቸው።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ለብዙ ጊዜ ከነበረው የጦርነትና ግጭት እንዲሁም የፀብ ሁኔታ ሁለት መቶ ሠላሳ ስምንት ዓመታት አለፉ።

፲፬ እናም እኔ ጄረም፣ ሰሌዳዎቹ ትንሽ በመሆናቸው፣ ከዚህ የበለጠ አልፅፍም። ነገር ግን እነሆ፣ ወንድሞቼ፣ ወደ ሌላኛው የኔፊ ሰሌዳዎች መሄድ ትችላላችሁ፤ እነሆ፣ በእነርሱ ላይ ይፃፉ ዘንድ ባደረጉት፣ ወይም እንደ ነገሥታቱ አፃፃፍ የጦርነት ታሪኮች ተቀርፀዋል።

፲፭ እናም እንደ አባቶቼ ትዕዛዛት መሰረት ይጠበቁ ዘንድ እነዚህን ሰሌዳዎች ለወንድ ልጄ፣ ለኦምኒ፣ አስረክባለሁ።