ቅዱሳት መጻህፍት
ያዕቆብ ፬


ምዕራፍ ፬

ነቢያት ሁሉ አብን በክርስቶስ ስም አመለኩ—የአብርሃም ይስሃቅን ለመሰዋት ማቅረቡ የእግዚአብሔርና የአንድያ ልጁ አምሳል ነበር—በኃጢያት ክፍያው ሰዎች እራሳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ አለባቸው—አይሁዶች የመሰረቱን ድንጋይ አይቀበሉም። ከ፭፻፵፬–፬፻፳፩ ም.ዓ. ገደማ።

አሁን እነሆ፣ እንዲህ ሆነ እኔ ያዕቆብ፣ ለህዝቤ በቃሌ ብዙ በማስተማሬ (እናም የእኛን ቃላት በሰሌዳዎቹ ላይ ለመቅረፅ ባለው ችግር የተነሳ፣ ከጥቂቶቹ ቃላቴ በስተቀር መፃፍ አልችልም) እናም በሰሌዳዎቹ ላይ የሚፃፉት ነገሮች መቅረት እንዳለባቸው እናውቃለን፤

ነገር ግን ከሰሌዳዎቹ ውጪ የፃፍናቸው ምንም አይነት ነገሮች መደምሰስና መጥፋት አለባቸው፤ ነገር ግን በሰሌዳዎቹ ላይ ለልጆቻችን፣ እናም ደግሞ ለተወደዱት ወንድሞቻችን፣ እኛን በሚመለከት ወይም አባቶቻቸውን በተመለከተ—በትንሽ ደረጃ እውቀት የሚሰጡትን፣ ጥቂት ቃላት መፃፍ እንችላለን—

አሁን በዚህ ነገር እንደሰታለን፤ እናም የተወደዱት ወንድሞቻችን እናም ልጆቻችን በምስጋና ልብ ይቀበሉት ዘንድ ተስፋ በማድረግ፣ እናም በደስታ እናም ያለማዘን፣ ያለንቀት ስለቀድሞ ወላጆቻቸው ለመማር ይመለከቱአቸው ዘንድ እነዚህን ቃላት በሰሌዳዎቹ ላይ ለመቅረፅ በትጋት እንሰራለን።

ስለክርስቶስ ማወቃችንን፣ እናም እርሱ ከመምጣቱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በክብሩ ተስፋ እንደነበር ያውቁ ዘንድ፣ ለዚህ ዓላማ እነዚህን ነገሮች ፃፍን፤ እናም የክብሩ ተስፋ የነበረን እኛ ብቻ ሳንሆን ነገር ግን ከእኛ በፊት የነበሩት ቅዱሳን ነቢያት ሁሉ ደግሞ ናቸው።

እነሆ፣ በክርስቶስ አምነዋል እናም አብንም በስሙ አምልከዋል፣ ደግሞም እኛ አብን በስሙ እናመልካለን። እናም ለዚህ ዓላማ የሙሴን ህግ እንጠብቃለን፣ ነፍሳችንን ወደእርሱ ያመለክታልና፤ እንዲሁም ከእግዚአብሔርና ከአንድያ ልጁ ጋር አምሳልነት ያለው፣ ለአብርሃም በምድረበዳ ልጁን ይስሀቅን ለመስዋዕት በማቅረብ ለእግዚአብሔር ትዕዛዝ ታዛዥ ሆኖ እንደተቆጠረለት፣ ለዚህም ምክንያት ይህም ለፅድቅ ለእኛ ተቀድሷል።

ስለሆነም፣ እኛ ነቢያትን እንመረምራለን፣ እናም ብዙ ራዕይና የትንቢት መንፈስ አለን፤ እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ስላሉንም ተስፋን እናገኛለን፣ እናም እምነታችን የማይናወጥ ሆኖ በእውነት በኢየሱስ ስም ስንገስፅ ያም ዛፉ፣ ወይንም ተራራው ወይም የባህሩ ሞገድ ይታዘዝልናል።

ይሁን እንጂ፣ በፀጋው እናም ለሰው ልጆች እራሱን ዝቅ በማድረጉ እነዚህን ነገሮች የማድረግ ኃይል እንዳለን እናውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር ድክመታችንን ያሳየናል።

እነሆ፣ የጌታ ስራ ታላቅና ድንቅ ነው። የእርሱ ሚስጥር ጥልቀት እንዴት የማይመረመር ነው፤ እናም ሰው የእርሱን መንገድ ሁሉ ፈልጎ ለማወቅ የማይቻል ነው። እናም ለእርሱ ካልተገለፀለት በቀር ማንም ሰው የእርሱን መንገድ አያውቅም፤ ስለሆነም፣ ወንድሞች፣ የእግዚአብሔርን ራዕይ አትናቁ።

እነሆም፣ ሰው በቃሉ ኃይል ወደ ምድር ፊት መጥቷል፣ ምድርም በቃሉ ኃይል ተፈጥራለች። ስለሆነም፣ እግዚአብሔር መናገር ከቻለና፣ እንዲሁም ዓለም ከተፈጠረ፣ እና እርሱ ሲናገር ሰው ከተፈጠረ፣ አቤቱ ምድርን ወይም በዚህ ፊት ያለው የእጁ ስራ እንደርሱ ፈቃድና ደስታ ማዘዝ አይችልምን?

ስለሆነም፣ ወንድሞቼ፣ ከእጁ ምክርን ለመቀበል እንጂ ጌታን ለመምከር አትሞክሩ። እነሆም፣ እናንተም በጥበብና፣ በፍርድ፣ እናም በታላቅ ምህረት፣ በስራው ላይ ሁሉ እንደሚመክር ታውቃላችሁ።

፲፩ ስለሆነም፣ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናም በክርስቶስ ባለው የትንሳኤ ኃይል መሰረት፣ ትንሳኤን ታገኙ ዘንድ፣ እናም እምነት በማግኘትና እራሱን በስጋ ከመግለጡ በፊት መልካም የሆነውን የክብሩን ተስፋ በማግኘት ለእግዚአብሔር የክርስቶስ የመጀመሪያው ፍሬ ሆናችሁ ትቀርቡ ዘንድ በአንድያ ልጁ፣ በክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ ከእርሱ ታረቁ።

፲፪ እናም አሁን፣ የተወደዳችሁ፣ እነዚህን ነገሮች ስነግራችሁ አትገረሙ፤ እናም የእርሱን ፍጹም እውቀት ለማወቅና፣ የትንሳኤንና የሚመጣው ዓለም እውቀትን ለማግኘት የክርስቶስን የኃጢያት ክፍያ ለምን አትናገሩም?

፲፫ እነሆ፣ ወንድሞቼ፣ ትንቢትን የሚናገር ሰዎች እንዲረዱት ዘንድ ትንቢት ይናገር፤ መንፈስ እውነቱን ይናገራል እንጂ አይዋሽምና። ስለሆነም፣ እርሱ ነገሮች በእርግጥ እንዳሉ፣ እናም ነገሮች በእርግጥ እንደሚሆኑ ይናገራል፤ ስለሆነም፣ እነዚህ ነገሮች ለነፍሳችን ደህንነት በግልፅ ተገልጠውልናል። ነገር ግን እነሆ፣ በእነዚህ ነገሮች እኛ ብቻ ምስክር አይደለንም፤ እግዚአብሔር ደግሞ ለጥንቶቹ ነቢያት ተናግሯቸዋልና።

፲፬ ነገር ግን እነሆ፣ አይሁዶች አንገተ ደንዳና ህዝቦች ነበሩ፣ እናም ግልፁን ቃላት ንቀዋል፣ ነቢያትን ገድለዋልም፣ መረዳት የማይችሉትን ነገሮች ተመኝተዋልም። ስለሆነም፣ በመታወራቸው ምክንያት፣ እውርነቱም የሚመጣው ከሚገባው በላይ በማተኮር ነው፤ እነርሱ ይወድቁ ዘንድ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ግልፅነቱን ከእነርሱ ወስዷልና፣ እናም ስለፈለጉት የማይረዱትን ብዙ ነገሮች ሰጥቷቸዋል። እናም እነርሱ ስለፈለጉት እግዚአብሔር አድርጎታል፣ ይህም እነርሱ ይሰናከሉበት ዘንድ ነው።

፲፭ እናም አሁን እኔ ያዕቆብ፣ ለመተንበይ በመንፈስ ተመርቻለሁ፤ በአይሁድ መሰናከልም፣ በእርሱም ላይ የሚገነቡትን እንዲሁም የደህንነት መሰረት የሚያገኙበትን አለቱን እንደማይቀበሉ በእኔ ባለው የመንፈስ ስራ ተረድቻለሁ።

፲፮ ነገር ግን እነሆ፣ እንደ ቅዱሳን መጽሐፍት መሰረት፣ ይህ አይሁዶች የሚገነቡበት አለት፣ ታላቅና የመጨረሻና፣ በብቻ የተረጋገጠ መሰረት ይሆናል።

፲፯ እናም አሁን፣ ወዳጆቼ፣ እርግጠኛውን መሰረት ከካዱ በኋላ፣ የማዕዘን ራስ ይሆን ዘንድ በእርሱ ላይ ለመመስረት እነርሱ እነዚህን እንዴት ማድረግ ይቻላቸዋል?

፲፰ እነሆ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ በምንም መንገድ ከመንፈሴ ፅኑነት ከተነቃነቅኩኝ እና ስለእናንተ ባለኝ ጭንቀት ምክንያት ካልተሰናከልኩኝ፣ ይህን ሚስጥር ለእናንተ እገልጥላችኋለሁ።