ቅዱሳት መጻህፍት
ያዕቆብ ፪


ምዕራፍ ፪

ያዕቆብ የሀብትን ፍቅር፣ ኩራትና፣ ምንዝርናን አወገዘ—ሰዎች ወገናቸውን ለመርዳት ሀብትን ሊሹ ይችላሉ—ጌታ ከኔፋውያን መካከል ማንኛውም ሰው ከአንድ በላይ ሚስት እንዳይኖረው አዘዘ—ጌታ በሴቶች ንፁህነት ይደሰታል። ከ፭፻፵፬–፬፻፳፩ ም.ዓ. ገደማ።

የኔፊ ወንድም ያዕቆብ፣ ኔፊ ከሞተ በኋላ ለኔፊ ህዝብ የተናገራቸው ቃላት—

አሁን፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እኔ ያዕቆብ እግዚአብሔር በሰጠኝ ሀላፊነት መሰረት፣ ሀላፊነቴን በጥሞና ለመወጣት፣ እናም ኃጢአታችሁንም ከመጎናፀፊያዬ አራግፍ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርንም ቃል ለእናንተ አውጅ ዘንድ በዚህ ቀን ወደ ቤተ መቅደስ መጣሁ።

እናም እስከዚህ ጊዜ ድረስ በተጠራሁበት ኃላፊነት ትጉህ እንደነበርኩ እናንተም ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን ባሁኑ ጊዜ ከዚህ ቀደም ከነበረኝ ይልቅ ለነፍሳችሁ ደህንነት ከፍተኛ ስሜትና ስጋት ተከፍቼአለሁ።

እነሆም፣ እስከዚህ ጊዜ ድረስ እኔ በሰጠኋችሁ፣ በጌታ ቃል ታዛዦች ነበራችሁ።

ነገር ግን እነሆ፣ እኔን አድምጡኝ፣ እናም ከሁሉም በላይ ሀይለኛ በሆነው የሰማይና የምድር ፈጣሪ ድጋፍ ሀሳባችንን በተመለከተ ልናገራችሁ እንደምችል፣ እንዴትስ ኃጢያትን መስራት እንደጀመራችሁ፣ ለእኔም በጣም የረከሰ እንደሆነ፣ አዎን፣ ለእግዚአብሔርም የረከሰ እንደሆነ እወቁ።

አዎን፣ ነፍሴን ያሳዝናል እናም የልባችሁን ክፋት በተመለከተ መመስከር ስላለብኝ፣ በፈጣሪዬ ፊት በእፍረት እንድሸማቀቅ ያደርገኛል።

እናም ደግሞ እናንተን በተመለከተ፣ የብዙዎቹም ስሜት በእግዚአብሔር ፊት፣ ለእግዚአብሔርም አስደሳች በሆኑት፣ እጅግ ለስላሳና ንፁህ፣ በቀላሉ ሊጎዱ በሚችል፣ በሚስቶቻችሁ እናም በልጆቻችሁ ፊት በኃይል መናገር ስላለብኝ አዝናለሁ፤

እናም እነርሱ አስደሳቹን የእግዚአብሔርን ቃል፣ አዎን፣ የቆሰለውን ነፍስ የሚፈውሰው ቃል ለመስማት ወደዚህ እንዲመጡ እገምታለሁ።

ስለሆነም፣ እንደወንጀላችሁ እናንተን ለመገሰፅ፣ የቆሰሉትን ቁስላቸው ለመዳንና ለመፈወስ ሳይሆን እንዲሰፋ ለማድረግ፤ እናም ያልቆሰሉት ደግሞ አስደሳቹን የእግዚአብሔር ቃል ከመጋበዝ ይልቅ ነፍሳቸውን ለመውጋት እናም በቀላሉ ሊጎዳ የሚችል አዕምሮአቸውን ለማቁሰል ከእግዚአብሔር በተቀበልሁት ጥብቅ ትዕዛዝ ምክንያትም በመገደዴ ነፍሴን ተጨቁኗል።

ነገር ግን ስራው ታላቅ ቢሆንም፣ በእግዚአብሔር ጥብቅ ትዕዛዝ መሰረት ማድረግ፣ እናም በልበ ንፁህና፣ በተሰበረ ልብ ፊት፣ እናም ሁሉን በሚገዛ አምላክ በሚቃኘው ዐይን ፊት ስለበደላችሁና ስለእርኩሰታችሁ መናገር አለብኝ።

፲፩ ስለሆነም፣ እንደእግዚአብሔር ቃል ግልፅነት እውነቱን ልነግራችሁ ይገባል። እነሆም ጌታን ስጠይቅ፣ ቃሉ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፥ ያዕቆብ ነገ ወደ ቤተ መቅደሱ ሂድ፣ እናም ለዚህ ህዝብ የምሰጥህን ቃል አውጅ።

፲፪ እናም አሁን እነሆ፣ ወንድሞቼ፣ ለእናንተ የማውጀው ቃል ይህ ነው፣ ብዙዎቻችሁ ወርቅና፣ ብር፣ እንዲሁም ለእናንተና ለዘሮቻችሁ የቃል ኪዳን ምድር በሆነችው በዚህች ምድር ውስጥ በይበልጥ የያዘችውን ሁሉንም ዓይነት የከበረ ብረት መፈለግ ጀምራችኋል።

፲፫ እናም የአምላክ እጅ በሰፊው ባርኳችኋል፣ ብዙ ሀብትንም አግኝታችኋል፤ አንዳንዶቻችሁም ከወንድሞቻችሁ በበለጠ ስለተቀበላችሁ በልባችሁ ኩራት ከፍ ብላችኋል፣ እናም በለበሳችሁትም ልብስ ውድነት አንገታችሁን አደንድናችኋል፣ ራሳችሁንም ከፍ አድርጋችኋል፣ እናም ራሳችሁን ከወንድሞቻችሁ የተሻላችሁ ስለሚመስላችሁ እነርሱን አሳዳችኋቸዋል።

፲፬ እናም አሁን፣ ወንድሞቼ፣ እግዚአብሔር በዚህ ነገር ከበደል ነጻ ያደርገናል ብላችሁ ትገምታላችሁን? እነሆ፣ አይሆንም እላችኋለሁ። ነገር ግን እርሱ ይፈርድባችኋል፣ እናም እናንተ በእነዚህ ነገሮች የምትቀጥሉ ከሆነ ፍርዱ በፍጥነት ይመጣባችኋል።

፲፭ አቤቱ መውጋት እንደሚችል፣ እናም በቅፅበት ዐይኑ ቅኝት ወደ አፈር ሊመታችሁ እንደሚችል ቢያሳያችሁ!

፲፮ አቤቱ ከክፋትና ከእርኩሰት ነፃ ቢያደርጋችሁ። እናም፣ አቤቱ የትዕዛዙን ቃል ብትሰሙና፣ ይህ የልባችሁ ክፋት ነፍሳችሁን እንዲያጠፋ ባትፈቅዱ!

፲፯ ወንድሞቻችሁ እንደ እራሳችሁ አስቡአቸው፣ እናም እነርሱም ልክ እንደ እናንተ ሀብታም ይሆኑ ዘንድ፣ ከሁሉም ጋር ተገናኚ እናም በንብረታችሁ ነፃ ሁኑ።

፲፰ ነገር ግን ሀብትን ከመፈለጋችሁ በፊት፣ የእግዚአብሔርን መንግስት ፈልጉ።

፲፱ እናም በክርስቶስ ተስፋን ካገኛችሁ በኋላ፣ የምትፈልጉአቸው ከሆነ ሀብትን ታገኛላችሁ፤ እነዚህንም መልካም ለማድረግ ዓላማ—የተራቆቱትን ለማልበስ፣ የተራቡትንም ለመመገብ፣ ምርኮኞችንም ነፃ ለማውጣት፣ እናም ለታመሙና ለተሰቃዩ ፋታን ለመስጠት ትፈልጓቸዋላችሁ።

እናም አሁን፣ ወንድሞቼ፣ ኩራትን በሚመለከት ተናግሬአችኋለሁ፤ እናም እግዚአብሔር በሰጣችሁ ነገሮች የተነሳ በልባችሁ ኩራት ጎረቤቶቻችሁን ያሰቃያችሁ፣ እንዲሁም ያሳደዳችሁ ስለዚህ ምን ትላላችሁ?

፳፩ እንዲህ አይነት ነገሮች ስጋን ሁሉ ለፈጠረው የረከሱ ናቸው ብላችሁ አታስቡምን? እናም አንዱ ፍጡር እንደሌላው በፊቱ የከበረ ነው። ሁሉም ስጋም ከአፈር ነው፤ እናም ትዕዛዛቱን ይጠብቁና እርሱን ለዘለዓለም ያከብሩት ዘንድ ለተመሳሳይ ዓላማ ፈጥሯቸዋል።

፳፪ እናም አሁን ይህን ኩራት በተመለከተ ለእናንተ ንግግሬን አቆማለሁ። እናም የከፋ ወንጀልን በተመለከተ ለእናንተ መናገር ባይኖርብኝ፣ ልቤ በእናንተ እጅግ ትደሰት ነበር።

፳፫ ነገር ግን በከፋው ወንጀላችሁ የተነሳ የእግዚአብሔር ቃል ከብዶኛል። እነሆም ጌታ እንዲህ ይላል—ይህ ህዝብ በክፋት ቀስ በቀስ ማደግ ይጀምራል፤ ቅዱሳት መጻሕፍትንም አይረዱም፣ ምክንያቱም የዳዊትንና ልጁ ሰለሞንን በተመለከተ በተፃፉት ነገሮች የተነሳ ዝሙትን በመፈፀማቸው ለእራሳቸው ምክንያትን ይፈልጋሉ።

፳፬ እነሆ፣ ዳዊትና ሰለሞን በእውነት ብዙ ሚስቶችና ዕቁባቶች ነበሩአቸው፣ ይህም በፊቴ የረከሰ ነበር ይላል ጌታ።

፳፭ ስለዚህ፣ ጌታ እንዲህ ይላል፣ ይህን ህዝብ ለራሴ ፃድቅ ቅርንጫፍ ከዮሴፍ የወገብ ፍሬ አስነሳ ዘንድ በኃያል ክንዴ ከኢየሩሳሌም ምድር አውጥቼዋለሁ።

፳፮ ስለሆነም፣ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ይህ ህዝብ እንደ ጥንቶቹ እንዲያደርግ አይፈቅድም።

፳፯ ስለሆነም፣ ወንድሞቼ እኔን ስሙኝ፣ እናም የጌታንም ቃል አድምጡ—በመካከላችሁ ከአንድ ሚስት በቀር ሌላ አይኑረው፤ እና ዕቁባቶች ምንም አይኑረው።

፳፰ እኔ ጌታ እግዚአብሔር በሴቶች ንፅህና እደሰታለሁና። እናም ማመንዘር በእኔ ፊት የረከሰ ነው፤ ይላል የሰራዊት ጌታ።

፳፱ ስለሆነም፣ ይህ ህዝብ ትዕዛዛቴን ይጠብቃል፣ ወይም ምድሪቱ በእነርሱ የተነሳ የተረገመች ትሁን ይላል የሰራዊት ጌታ።

እኔ ለራሴ ዘርን ለማቆም ከፈለኩኝ፣ ህዝቤን አዛለሁ፤ አለበለዚያ እነርሱ እነዚህን ነገሮች ያዳምጣሉ ይላል የሰራዊት ጌታ።

፴፩ እነሆ እኔ ጌታ በኢየሩሳሌም ምድር ውስጥ፣ አዎን፣ እናም በህዝቤ ምድር ሁሉ፣ በባሎቻቸው ክፋትና እርኩሰት የተነሳ የህዝቤን ሴት ልጆች ሀዘንን ተመልክቻለሁ፣ እናም ልቅሶአቸውን ሰምቻለሁ።

፴፪ እናም የሰራዊት ጌታ፣ ከኢየሩሳሌም ምድር እንዲወጡ ያደረኩአቸው፣ የዚህ ህዝብ መልካም ሴት ልጆች ጩኸት ወደ እኔ በህዝቤ ወንዶች ላይ ይመጣ ዘንድ አልፈቅድም ይላል የሰራዊት ጌታ።

፴፫ በከባድ እርግማን፣ እንዲሁም ለጥፋታቸውም፣ ካልጎበኘኋቸው በቀር የህዝቤ ሴት ልጆች በሩህሩህነታቸው የተነሳ በምርኮ አይወሰዱም፤ ምክንያቱም እነርሱ ዝሙትን እንደጥንቶቹ አይፈፅሙም ይላል የሰራዊት ጌታ።

፴፬ እናም አሁን እነሆ፣ ወንድሞቼ፣ እነዚህ ትዕዛዛት ለአባታችን ሌሂ ተሰጥተውት እንደነበር ታውቃላችሁ፤ ስለሆነም በፊትም ታውቋቸዋላችሁ፤ እናም ማድረግ የማይገባችሁን እነዚህን ነገሮች በማድረጋችሁ ለታላቅ እርግማን መጥታችኋል።

፴፭ እነሆ፣ ከወንድሞቻችን ከላማናውያን የበለጠ በደል ሰርታችኋል። በእነርሱም ፊት መጥፎ ምሳሌዎች በመሆናችሁ፣ የሩህሩህ ሚስቶቻችሁን ልብም ሰብራችኋል፣ የልጆቻችሁንም መተማመን አጥታችኋል፤ እናም በልባቸው ጥልቅ ሀዘን በእናንተ ላይ ወደ እግዚአብሔር መጥተዋል። እናም በእናንተ ላይ በሚወርደው በእግዚአብሔር ቃል ጥብቅነት የተነሳ፣ ብዙ ልቦች በሀዘን ቆሰሉ በጥልቅ ቁስልም ተበሱ።