ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፷፩


ምዕራፍ ፷፩

ፓሆራን በመንግስት ላይ ስለሆነው ሁከት፣ እና አመፃ ለሞሮኒ ነገረው—የንጉሱ ሰዎች ዛራሔምላን ያዙ፣ እናም ከላማናውያን ጋር አንድ ቡድን ሆኑ—ፓሆራን በአማፅያኑ ላይ ወታደራዊ እርዳታን ጠየቀ። በ፷፪ ም.ዓ. ገደማ።

እነሆ እንዲህ ሆነ ሞሮኒ ለዋናው ገዢ ደብዳቤውን ከላከ በኋላ፣ ወዲያውኑ ከዋናው ገዢ ፓሆራን ደብዳቤ ደረሰው። እናም የተቀበለው ቃል እንዲህ ይላል፥

እኔ ፓሆራን የዚህች ምድር ዋና ገዢ የሆንኩ፣ በሠራዊቱ ሊቀ ሻምባል ለሆነው ሞሮኒ ይህንን መልዕክት ልኬአለሁ። እነሆ፣ ሞሮኒ እልሀለሁኝ፣ በታላቁ ስቃይህ አልደሰትም፤ አዎን፣ ይህ ነፍሴን ያሳዝናታል።

ነገር ግን እነሆ፣ በስቃይህ የሚደሰቱት አሉ፣ አዎን፣ በእኔ እናም የነጻነት ሰዎች በሆኑት ህዝቦቼ ላይ በአመፅ ተነስተዋል፣ አዎን፣ ለአመፅ የተነሱት በቁጥር እጅግ ብዙ ናቸው።

እናም የፍርዱን ወንበር ከእኔ ለመውሰድ የፈለጉት የዚህ የታላቁ ክፋት መንስኤ ናቸው፤ ምክንያቱም ታላቅ የሽንገላ ቃላት ተጠቅመዋል፣ እናም በመካከላችን የአደገኛ ስቃይ መንስኤ እንዲሆን የብዙዎችን ልብ ለውጠዋል፤ ስንቆቻችንን ይዘውብናልና፣ ወደ አንተም እንዳይመጡ ነፃ የሆኑትን ሰዎቻችንን አስፈራርተውብናል።

እናም እነሆ፣ ከፊታቸው እኔንም አባረውኛል፣ እናም ከእኔጋ ለማግኘት ከምችላቸው ያህል ሰዎች ጋርም ወደ ጌዴዎን ምድር ሸሽቻለሁ።

እናም እነሆ፣ በዚች ምድር አዋጅ ልኬአለሁ፤ እናም እነሆ ሀገራቸውንና ነፃነታቸውን ለመከላከልና፣ ስህተቶቻችንንም ለመበቀል የጦር መሳሪያቸውን ለማንሳት በየቀኑ ወደእኛ ይሰበሰባሉ።

እናም በእኛ ላይ ለአመፅ የተነሱት፣ አዎን፣ እነርሱ እስከሚፈሩን፣ እናም ለውጊያ በእኛ ላይ ለመምጣት እስከማይደፍሩም ድረስ ወደ እኛ መጥተዋል።

ምድሪቱን እንዲሁም የዛራሔምላ ከተማን ይዘዋል፤ በእነርሱም ላይ ንጉሥን ሹመዋል፣ እናም ለላማናውያን ንጉስም ጽፏል፣ በዚህም ከእርሱ ጋር አንድነት ኖሯቸዋል፤ በዚህም አንድነት የዛራሔምላን ከተማ ለማስተዳደር ተስማማ፤ በሚያስተዳድርበት ጊዜም ላማናውያን የተቀረውን ምድር ያሸንፋሉ፤ እናም በላማናውያን በተሸነፉ ጊዜም በህዝቡ ላይ ንጉስ በመሆንም ይሾማል በማለት ገምቶ ነበር።

እናም እንግዲህ፣ በደብዳቤህ ላይ ወቅሰኸኛል፣ ነገር ግን ይህ ምንም አይደለም፣ እኔም አልተቆጣሁም፣ ነገር ግን ከልብህ ታላቅነት ተደስቻለሁ። እኔ ፓሆራን የህዝቤን መብትና ነፃነት የምጠብቅበትን የፍርድ ወንበሬን ብቻ ከመመለስ በቀር ስልጣንን አልፈልግም። እግዚአብሔር ነፃ ባደረገን በዚያ ነፃነት ህይወቴ ትፀናለች።

እናም እንግዲህ፣ እነሆ፣ ኃጢያትን ደም እስከሚፈስ ድረስ እንቃወማለን። ላማናውያን በምድራቸው የሚቆዩ ከሆነ ደማቸውን አናፈሰውም።

፲፩ ወንድሞቻችን በአመፅ ካልተነሳሱ፣ እናም ጎራዴአቸውን በእኛ ላይ ካላነሱ ደማቸውን አናፈስም።

፲፪ በእግዚአብሔር ፍርድ አስፈላጊ ከሆነ እንዲሁም እርሱ እንድናደርገው ካዘዘን እራሳችንን በባርነት ቀንበር ስር ማድረግ ይኖርብናል።

፲፫ ነገር ግን እነሆ እግዚአብሔር እራሳችንን በጠላቶቻችን ስር እንድናደርግ አያዘንም፤ ነገር ግን እምነታችንን በእርሱ ላይ ማድረግ አለብን፣ እናም እርሱ ያድነናል።

፲፬ ስለዚህ፣ የተወደድክ ወንድሜ፣ ሞሮኒ፣ ክፋትን እንቃወም፣ እናም በቃል ለመቃወም የማንችላቸውን ክፉቶችን፣ አዎን፣ እንደሚያምጹትና ከእኛ እንደሚገነጠሉት አይነት፣ ነፃነታችንን እናገኝ ዘንድ፣ በቤተክርስቲያን ታላቅ ጥቅም እናም በአዳኛችንና በአምላካችን እንደሰት ዘንድ፣ እነርሱን በጎራዴዎቻችን እንቃወማቸው

፲፭ ስለዚህ፣ ከጥቂት ሰዎችህ ጋር በፍጥነት ወደ እኔ ና፣ እናም የቀሩትን በሌሂና በቴአንኩም ትዕዛዝ ስር እንዲሆኑ ተዋቸው፤ በእግዚአብሔር መንፈስ መሰረት፣ ደግሞም በእነርሱ ውስጥ ባለው የነፃነት መንፈስ በዚያ ምድር ጦርነቱን እንዲመሩ ስልጣንን ስጣቸው።

፲፮ እነሆ አንተ ወደ እኔ እስከምትመጣ ድረስ እንዳይጠፉ ጥቂት ስንቅ ልኬላቸዋለሁ።

፲፯ ወደዚህ ስፍራ ለዘመቻህ ያለህን ኃይል በሙሉ በአንድነት አሰባስብ፤ እናም በአምላካችን ባለን እምነት በኃይል በተቃዋሚዎቹ ላይ በፍጥነት እንሄዳለን።

፲፰ እናም ወደ ሌሂና ቴአንኩም ለመላክ ተጨማሪ ስንቅ እናገኝ ዘንድ የዛራሔምላን ከተማ እንወስዳለን፤ አዎን፣ በጌታ ኃይልም በእነርሱ ላይ እንሄዳለን፣ እናም ለዚህ ታላቅ ጥፋትም ፍፃሜ እንዲሆን እናደርጋለን።

፲፱ እናም እንግዲህ፣ ሞሮኒ፣ በወንድሞቻችን ላይ መዝመት ትክክል ይሁን አይሁን ምን ማድረግ እንዳለብኝ በመጠኑ ተጨንቄ ስለነበር፣ ደብዳቤህን በማግኘቴ ተደስቻለሁ።

ነገር ግን ንስሃ ካልገቡ በእነርሱ ላይ መሄድ አለባችሁ በማለት ጌታ እንዳዘዘህ ተናግረሃል።

፳፩ የሌሂንና፣ ቴአንኩምን እምነት ማጠናከርን አረጋግጥ፤ እንዳይፈሩ ንገራቸው፤ እነርሱን፤ አዎን፣ እናም ደግሞ እግዚአብሔር ባደረጋቸው ነፃነት የሚጸኑትን ያድናልና። እናም እንግዲህ ለተወደደው ወንድሜ ሞሮኒ ደብዳቤዬን አበቃለሁ።