ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፵፭


ሔለማን በዘመኑ ባስቀመጠው በምዝገባው መሰረት በሔለማን ዘመን የኔፊ ህዝብ የጦርነታቸው እና የፀባቸው ታሪክ።

ከምዕራፍ ፵፭ እስከ ፷፪ አጠቃሎ የያዘ።

ምዕራፍ ፵፭

ሔለማን የአልማን ቃላት አመነ—አልማ ስለኔፋውያን ጥፋት ተነበየ—እርሱም ምድሪቱን ባርኳታል፣ እናም ረግሟታል—አልማ ምናልባት እንደሙሴ በመንፈስ ተወስዷል—ፀብ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ አደገ። በ፸፫ ም.ዓ. ገደማ።

እነሆ፣ አሁን እንዲህ ሆነ የኔፊ ህዝብ ጌታ በድጋሚ ከጠላቶቻቸው እጅ እንዲወጡ ስላደረጋቸው እጅግ ተደሰቱ፤ ስለዚህ ለጌታ ለአምላካቸው ምስጋናን አቀረቡ፤ አዎን፣ እናም እጅግ ፆሙና፣ ፀለዩም፣ እግዚአብሔርን እጅግ ታላቅ በሆነ ደስታ አመለኩትም።

እናም እንዲህ ሆነ በኔፊ ሕዝብ በመሣፍንቱ የአስራ ዘጠነኛው የንግስ ዘመን ላይ አልማ ወደ ልጁ ሔለማን መጣ እናም እንዲህ አለ፥ ስለተጠበቁት መዝገቦች በተመለከተ የተናገርኳቸውን ቃላት ታምናለህን?

እናም ሔለማን እንዲህ ሲል ተናገረው፥ አዎን አምናለሁ።

እናም አልማ በድጋሚ እንዲህ አለ፥ በሚመጣው በክርስቶስ ታምናለህን?

እናም እርሱ እንዲህ አለ፥ አዎን፣ የተናገርካቸውን ቃላት በሙሉ አምናለሁ።

እናም አልማ በድጋሚ እንዲህ አለው፥ ትዕዛዛቴን ትጠብቃለህን?

እናም እርሱ እንዲህ አለ፥ አዎን፣ ትዕዛዛቶችህን በልቤ ሙሉ እጠብቃቸዋለሁ።

ከዚያም አልማ እንዲህ አለው፥ አንተ የተባረክህ ነህ፤ እናም ጌታ በዚህች ምድር ላይ እንድትበለፅግ ያደርግሃል።

ነገር ግን እነሆ፣ ለአንተ በመጠኑ የምተነብየው ነገር አለኝ፤ ነገር ግን ለአንተ የምተነብየውን ለሰዎች አታሳውቅ፤ አዎን፣ የምተነብይልህን ትንቢት እስከሚፈፀም ድረስ ማንም እንዲያውቀው አታድርግ፤ ስለዚህ የምነግርህን ቃላት ፃፍ።

እናም ቃላቱ እነኚህ ናቸው፥ እነሆ፣ እነዚህ ህዝብ፣ ኔፋውያን፣ በውስጤ ባለው የራዕይ መንፈስ መሰረት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱን ከገለፀላቸው ከአራት መቶ ዓመታት በኋላ እምነትን በማጣት እንደሚመነምኑ እመለከታለሁ።

፲፩ አዎን፣ እናም ከዚያም፣ የኔፊ ህዝብ እስከሚጠፉም ድረስ፣ ጦርነትና ቸነፈርን ይመለከታሉ፤ አዎን፣ በመሃከላቸው ረሃብ እና የደም መፋሰስ ይሆናል—

፲፪ አዎን፣ ይህም የሆነው እምነት በማጣት በመመንመናቸውና በጨለማው ስራና በአመንዝራነት፣ እናም በሁሉም ዓይነት ክፋቶች ላይ በመውደቃቸው ነው፤ አዎን፣ እንዲህ እልሃለሁ፣ በታላቁ ብርሃንና ዕውቀት ላይ ኃጢያትን በመፈፀማቸው፤ አዎን፣ ይህ ታላቅ ክፋት ከመምጣቱ በፊት አራተኛው ትውልድም ቢሆን አያልፍም እላችኋለሁ።

፲፫ እናም ያ ታላቁ ቀን ሲመጣ፣ እነሆ፣ አሁን ያሉት፣ ወይንም ከኔፊ ህዝብ ጋር አብረው የተቆጠሩት ወገኖች ከኔፊ ህዝብ ጋር የማይቆጠሩበት ጊዜ በፍጥነት ይመጣል።

፲፬ ነገር ግን ማንም የተረፈ፣ እናም በዚያን ታላቁና ከአስፈሪው ቀን ያልጠፋ፣ የጌታ ደቀ መዝሙር ተብለው ከሚጠሩት ጥቂቶች በስተቀር፣ ከላማናውያን ጋር አብሮ ይቆጠራልና፣ እንደ እነርሱም ይሆናሉ፤ እናም ላማናውያን እነርሱን እስከሚጠፉ ድረስም እንኳን ያሳድዷቸዋል። እናም እንግዲህ፣ በኃጢያትም የተነሳ ይህ ትንቢት ይፈፀማል።

፲፭ እናም አሁን እንዲህ ሆነ አልማ እነዚህን ነገሮች ለሔለማን ከተናገረ በኋላ፣ ባረከው፣ እናም ደግሞ ሌሎች ወንድ ልጆቹን ባረካቸው፤ ደግሞም ለፃድቃኖች ሲል ምድሪቱን ባረካት።

፲፮ እናም እንዲህ አለ፥ ጌታም እንዲህ ይላል—አዎን፣ ይህች ምድር ጥፋት ለሚያደርጉት ለሁሉም ሀገር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ህዝብ በሙሉ ሲበስሉ እንዲጠፉ ዘንድ ምድሪቱ የተረገመች ትሁን፤ እናም እንደተናገርኩትም ይሆናል፤ ይህ ለምድሪቱ የእግዚአብሔር እርግማን እንዲሁም በረከት ነው፤ ምክንያቱም ጌታ ኃጢያትን በትንሹም ቢሆን ሊቀበለው አይቻለውምና።

፲፯ እናም እንግዲህ አልማ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ ቤተክርስቲያኗን ባረካት፤ አዎን፣ ከዚህ ጊዜም ጀምሮ በእምነት በመፅናት የቆሙትን በሙሉ ባረካቸው።

፲፰ እናም አልማ ይህንን ባደረገ ጊዜ፣ ወደ ሜሌቅ ምድር እንደሚሄድ በማድረግ፣ ከዛራሔምላ ምድር ወጣ። እናም እንዲህ ሆነ ከዚህም በኋላ ከእርሱ ምንም አልተሰማም ነበር፤ ስለሞቱም ሆነ ቀብሩ ምንም አላወቅንም።

፲፱ እነሆ፣ እርሱ ፃድቅ ሰው መሆኑን ይህን እናውቃለን፤ እናም በመንፈስ መወሰዱን ወይንም በጌታ እጅ እንደሙሴ መቀበሩ በቤተክርስቲያን ይህ ንግግር ተሰራጨ። ነገር ግን እነሆ ቅዱሳት መጻሕፍት ጌታ ሙሴን ለራሱ ወሰደው ይላሉ፤ እናም አልማንም ደግሞ በመንፈስ ወደ እርሱ ወስዶታል ብለን እንገምታለን፤ ስለዚህ በዚህ የተነሳ ስለአልማ ሞትም ሆነ ቀብር ምንም አናውቅም።

እናም አሁን እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ የአስራ ዘጠነኛ ንግስና መጀመሪያ ላይ ሔለማን በህዝቡ መካከል ቃሉን ለማወጅ ሄደ።

፳፩ እነሆም ህዝቡ ከላማናውያን ጋር በመዋጋቱና፣ ትንሽ ፀብና ርበሻ በህዝቡ መካከል በመኖሩ፣ የእግዚአብሔር ቃል በመካከላቸው መነገሩ አስፈላጊ እየሆነ፣ አዎን፣ እናም በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ደንብ መቋቋሙ አስፈላጊ እየሆነ መጣ።

፳፪ ስለዚህ፣ ሔለማንና ወንድሞቹ በምድሪቱ ላይ፣ አዎን፣ በምድሪቱ ላይ ባሉት በኔፊ ሰዎች በተያዙት ከተሞች ሁሉ ቤተክርስቲያኗን በድጋሚ ለማቋቋም ሄዱ። እናም እንዲህ ሆነ በምድሪቱ ላይ ባሉት በቤተክርስቲያኖቹ በሙሉ ካህናትን እና መምህራንን ሾሙአቸው።

፳፫ እናም አሁን እንዲህ ሆነ ሔለማንና ወንድሞቹ በቤተክርስቲያኖቹ ላይ ካህናትንና መምህራንን ከሾሙ በኋላ በህዝቡ መካከል ፀብ ተነሳ፣ እናም የሔለማንና የወንድሞቹንም ቃላት አላዳመጡም።

፳፬ ነገር ግን በትዕቢት እያደጉ፣ እጅግ ሀብታሞችም በመሆናቸው በልባቸው ኩራት እየተሞሉ ሄዱ፤ ስለዚህ በራሳቸው ግምት ከፍ ብለው በልፅገዋል፤ እናም በእግዚአብሔር ፊት በቅንነት ለመራመድ የሔለማንንና የወንድሞቹን ቃላት አላዳመጡም።