ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፴፯


ምዕራፍ ፴፯

የነሐስ ሰሌዳዎች እናም ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ነፍሳትን ወደ ደህንነት ለማምጣት ተጠበቁ—ያሬዳውያን በክፋታቸው የተነሳ ጠፉ—ሚስጥራዊው መሐላቸው እና ቃል ኪዳናቸው ከህዝቡ መጠበቅ አለበት—በስራችሁም ሁሉ ከጌታ ጋር ተማከሩ—ሊያሆና ኔፋውያንን እንደመራቸው የክርስቶስ ቃልም ሰዎችን ወደ ዘለዓለማዊው ህይወት ይመራቸዋል። በ፸፬ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን፣ ልጄ ሔለማን፣ ለእኔ በአደራ የተሰጠኝን መዛግብት እንድትወስድልኝ አዝሃለሁ፤

እናም ደግሞ በኔፊ ሰሌዳ ላይ ያለውን የዚህን ህዝብ ታሪክ እኔ እንዳደረግሁት እንድትጠብቅ አዝሀለሁ፣ እናም እኔ የጠበቅኋቸውን እነዚህን ቅዱስ ነገሮች ሁሉ እኔ እንደጠበቅኋቸው አድርግ፤ ምክንያቱም እነዚህ የተጠበቁት ለመልካም ዓላማ ነውና።

እናም እነዚህን ፅሁፎች የያዙት፣ የቅዱሱን መጻሕፍት ታሪክ የያዙትን፣ የጥንት ቅድመ አባቶቻችንን የትውልድ ሀረግ ከመጀመሪያው ጀምሮ የያዙትን፣ እነዚህ የነሐስ ሰሌዳዎች

እነሆ፣ እነዚህ ነገሮች ተጠብቀው ከአንዱ ትውልድ ወደሌለኛው እንዲተላለፉ፣ እናም ለሁሉም ሀገር፣ ነገድ፣ ቋንቋ፣ እና ህዝብ እስኪደርሱ በውስጣቸው ያለውን ሚስጥር እንዲያውቁ በጌታ እጅ መቀመጥ እንዳለባቸው በአባቶቻችን ተተንብዮአል።

እናም አሁን እነሆ፣ ከተጠበቁም ብሩህነታቸውን ይዘው መቀጠል አለባቸው፤ አዎን፣ እናም እነርሱም፣ አዎን፣ ደግሞም ቅዱስ ፅሑፍ የሆኑትን የያዙ ሰሌዳዎችም ብሩህነታቸውን ይዘው ይቀጥላሉ።

አሁን ይህ በእኔ ውስጥ ያለ ሞኝነት ነው በማለት ትገምት ይሆናል፤ ነገር ግን እነሆ እንዲህ እልሀለሁ፥ በትንሽና በቀላል ነገሮች ታላቅ ነገሮች ተፈፅመዋል፤ እናም ቀላል መንገዶች ብዙውን ጊዜ ጥበበኞችን ያሳፍራሉ።

እናም ጌታ እግዚአብሔር ታላቁንና ዘለዓለማዊ አላማውን ለማምጣት በእነዚህ መንገዶች ይሰራል፤ እናም በጣም ቀላል በሆነ መንገድ ጌታ ጥበበኞችን ያሳፍራልና፣ የብዙ ሰዎችን ነፍስ ወደ ደህንነት ያመጣል።

እናም አሁን፣ እስከአሁን ድረስ እነዚህ ነገሮች እንዲጠበቁ በእግዚአብሔር ጥበብ ሆኖ ቆይቷል፤ እነሆ፣ የዚህን ህዝብ ትዝታ አስፍተዋል፣ አዎን፣ እናም ብዙ የጎዳናዎቻቸውን ተሳሳችነት አሳምነዋል፣ እናም ለነፍሳቸው ደህንነትም እግዚአብሔርን እንዲያውቁ አድርጓቸዋል።

አዎን፣ እኔ እንዲህ እላችኋለሁ፥ በእነዚህ ሰሌዳዎች ላይ በሚገኙት እነዚህ መዝገቦች ውስጥ ከሚይዟቸው በእነዚህ ነገሮች ባይሆን ኖሮ አሞንና ወንድሞቹ ብዙ ሺህ ላማናውያንን የአባቶቻቸው ወግ የተሳሳተ እንደሆነ ሊያሳምኑአቸው አይችሉም ነበር፤ አዎን፣ እነዚህ ታሪኮች እና ቃላቶቻቸው ወደንስሃ አመጡአቸው፤ ይህም ማለት፣ ጌታ አምላካቸውን እንዲያውቁ እናም በአዳኛቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ሐሴትን እንዲያደርጉ አደረጉአቸው።

እና፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እነዚህን፣ አዎን፣ እናም ደግሞ፣ አሁን በኃጢያትና በክፋት ልባቸውን የሚያጠጥሩትን አንገተ ደንዳና የሆኑ ኔፋውያን ወንድሞቻችንን አዳኙን ወደ ማወቅ እንደሚያመጡ ማን ያውቃል?

፲፩ አሁን እነዚህ ሚስጥሮች ሙሉ በሙሉ ለእኔ አልታወቁኝም፤ ስለዚህ ይበልጥ ከመናገር ልቆጠብ።

፲፪ እናም በእግዚአብሔር ለሚታወቀው ዓላማ፣ ለመልካም ዓላማ ተጠበቁ ብቻ ካልኩኝ ይበቃኛል፤ ምክንያቱም በስራዎቹ ሁሉ በጥበብ ይመክራልና፣ እናም ጎዳናው ቀጥተኛ መንገዱም አንድ ዘለዓለማዊ ዙሪያ ነው።

፲፫ አስታውስ ልጄ ሔለማን ሆይ፣ የእግዚአብሔር ትዕዛዛት እንዴት ጥብቅ እንደሆኑ አስታውስ። እናም እርሱ እንዲህ ብሏል፥ ትዕዛዛቴን ከጠበቅህ በምድሪቱ ላይ ትበለፅጋለህ—ነገር ግን ትዕዛዛቱን ካልጠበቅህ ከፊቱ ትለያለህ።

፲፬ እናም ልጄ አሁን ጌታ ቅዱስ የሆኑትን፣ ቅዱስ አድርጎ የጠበቃቸውን እናም ደግሞ ለወደፊቱም ትውልድም ኃይሉን ያሳይበት ዘንድ ለመልካም ዓላማው የሚጠብቃቸውን እነዚህን ነገሮች በአደራ እንደሰጠህ አስታውስ።

፲፭ እናም አሁን እነሆ፣ በትንቢት መንፈስ እናገርሃለሁ፤ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የምትተላለፍ ከሆነ፣ እነሆ፣ እነዚህ ቅዱስ የሆኑት ነገሮች በእግዚአብሔር ኃይል ይወሰዱብሃል፣ እናም በንፋሱ ፊት እንዳለ ገለባ እንዲያበጥርህ ለሰይጣን ይሰጥሃል።

፲፮ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ከጠበቅህ፣ እናም በእነዚህ ቅዱስ ነገሮች እግዚአብሔር ባዘዘህ መሰረት ከሰራህ (በምታደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ወደ ጌታ አቤት እንድትል ይገባልና) እነሆ ከአንተ ሊወስድብህ የሚችል ምንም ኃይል፣ የምድርም ሆነ የሲኦል፣ አይኖርም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ቃሉን ሁሉ ይፈፅም ዘንድ ኃያል ነውና።

፲፯ ለአንተ የገባውን ቃል ኪዳን በሙሉ ይፈፅማልና፣ ለአባቶቻችን የገባውን ቃል ኪዳንም ይፈፅማልና።

፲፰ ኃይሉን ለሚመጣው ትውልድ ያሳይ ዘንድ፣ እነዚህን ነገሮች ለመልካም ዓላማው እንደሚጠብቃቸው ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋልና።

፲፱ እናም አሁን እነሆ፣ ብዙ ሺህ ላማናውያንን እውነትን እንዲያውቁ በመመለስ አንዱን ዓላማውን ፈፅሟል፤ በእነርሱም ኃይሉን አሳይቷል፤ እናም ለሚመጣው ትውልድም ደግሞ አሁንም በእነርሱ ኃይሉን ያሳያል፤ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ይጠበቃሉ።

ስለዚህ ልጄ ሔለማን ቃሌን በመፈፀም ትጉህ እንድትሆን እናም እንደተፃፉት የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በመጠበቅ ትጉህ እንድትሆን አዝሃለሁ።

፳፩ እናም አሁን፣ ሀያ አራቱን ሰሌዳዎች በተመለከተ፣ ሚስጥሮችንና፣ የጨለማው ስራ፣ እናም የእነርሱን ሚስጥራዊ ስራ፣ ወይም የጠፉት ሰዎች የሚስጥር ስራ ለዚህ ህዝብ ይገለጥ ዘንድ እንድትጠብቃቸው እናገራለሁ፤ አዎን፣ ግድያቸውን ሁሉና፣ ስርቆታቸውንና፣ ዝርፊያቸውንና፣ ክፋታቸውንና፣ እርኩሰታቸውን ሁሉ ለዚህ ህዝብ ይገልጡ ዘንድ፤ አዎን፣ እናም እነዚህን መተርጎሚያዎች አስቀምጥ።

፳፪ እነሆም፣ ጌታ ይህ ህዝብ በጨለማው መሥራት፣ አዎን፣ ሚስጥራዊ ግድያንና እርኩሰትን፣ ሲጀምር ተመለከተ፤ ስለዚህ ጌታ እንዲህ ይላል፥ ንስሃ የማይገቡ ከሆነ ከምድር ገፅ ይጠፋሉ።

፳፫ እናም ጌታ እንዲህ ይላል፥ ለአገልጋዬ ጋዜሌም፣ በጨለማ በብርሃን የሚያንፀባርቀውን ድንጋይ አዘጋጅለታለሁ፤ እኔን ላገለገሉኝም እገልፅላቸዋለሁ፣ የወንድሞቻቸውንም ስራ፣ አዎን፣ ሚስጥራዊ ስራቸውን፣ የጨለማ ስራቸውንና ክፋታቸውን፣ እናም እርኩሰታቸውን አሳያቸዋለሁ።

፳፬ እናም አሁን፣ ልጄ፣ እነዚህ ተርጓሚዎች ጌታ እንዲህ በማለት የተናገረውን ቃላት ይፈፀሙ ዘንድ ተዘጋጅተዋል፥

፳፭ ሚስጥራዊ ስራዎቻቸውን እና እርኩሰታቸውን ከጨለማው ወደ ብርሃኑ አመጣዋለሁ፤ እናም ንስሃ ካልገቡ ከምድረ ገፅ አጠፋቸዋለሁ፤ እናም ሁሉ ከዚህ በኋላ ምድሪቷን የራሳቸው ለሚያደርጉ ሀገሮች ሁሉ ሚስጥራቸውንና እርኩሰታቸውን ወደ ብርሃን አመጣለሁ።

፳፮ እናም አሁን፣ ልጄ፣ እነርሱ ንስሃ እንዳልገቡ እናያለን፤ ስለዚህም ጠፍተዋል፤ እናም እስከዚህ ድረስ የእግዚአብሔር ቃል ተፈፅሟል፤ አዎን ሚስጥራዊው እርኩሰታቸው ከጨለማው ወጥቷል እናም እኛ እንድናውቀው ተደርጓል።

፳፯ እናም እንግዲህ፣ ልጄ፣ መሃላዎቻቸውን፣ ቃል ኪዳናቸውንና፣ ሚስጢራዊ የሆነውን የእርኩሰታቸውን ስምምነት ሁሉ እንድትጠብቅ አዝሀለሁ፤ አዎን እናም ምልክቶቻቸውንና አስደናቂ ነገሮቻቸውን ሁሉ እንዳያውቋቸው ከእነዚህ ሰዎችም ትጠብቃለህ፤ አለበለዚያ በጨለማው ውስጥ እነርሱ ይወድቁ ይሆናል፣ እንዲሁም ሊጠፉ ይችላሉና።

፳፰ እነሆ የጨለማ ሠራተኞቹም በክፋት ሙሉ በሙሉ ባደጉ ጊዜ በእግዚአብሔር ኃይል መሰረት የጭለማ ስራን በሚሰሩት ላይ ሁሉ ጥፋት እንደሚመጣባቸው በምድሪቱ ላይ ሁሉ እርግማን አለ፤ ስለሆነም እነዚህ ሰዎች እንዳይጠፉ እመኛለሁ።

፳፱ ስለዚህ ከዚህ ህዝብ ይህንን የመሃላቸውንና የቃል ኪዳናቸውን ሚስጥራዊ እቅድ ትጠብቃለህ፣ እናም ክፋታቸውንና፣ ግድያቸውን፣ እንዲሁም እርኩሰታቸውን ብቻ ለእነርሱ እንዲታወቁ አድርግ፤ እናም እንደዚህ ዓይነቱን ኃጢያትና፣ እርኩሰት፣ እንዲሁም ግድያ እንዲጠሉ አስተምራቸው፤ እናም ደግሞ ይህ ህዝብ በክፋቱና በእርኩሰቱ፣ እንዲሁም በመግደሉ ምክንያት እንደጠፉ አስተምራቸው።

እነሆም ስለኃጢአታቸው ለመናገር ከእነርሱ መካከል የመጡትን የጌታን ነቢያት በሙሉ ገደሉአቸው፤ እናም የተገደሉት ደም በገደሉአቸው ላይ ወደ ጌታ አምላካቸው ለበቀል ጮኸ፤ እናም የእግዚአብሔር ፍርድ በጨለማው ሰራተኞችና፣ በሚስጥራዊው ሴራዎች ላይ እንደዚህ መጣ።

፴፩ አዎን፣ እናም ሁሉም በክፋት ከማደጋቸው በፊት ንስሃ ካልገቡ በስተቀር፣ በጨለማው ሰራተኞች፣ እናም በሚስጥራዊው ሴራዎች ላይ ለጥፋትም እንኳን ምድሪቱ ለዘለዓለም ረገማት።

፴፪ እናም አሁን፣ ልጄ፣ የተናገርኩህን ቃላት አስታውስ፤ ሚስጥራዊ ዕቅድን ለህዝቡ በአደራ ለመስጠት አትመን፣ ነገር ግን በኃጢያት እና በክፋት ላይ ዘለዓለማዊ ጥላቻን አስተምራቸው።

፴፫ ንስሃን እናም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እምነትን ስበክላቸው፤ እራሳቸውን ዝቅ እንዲያደርጉና፣ የዋህ፣ እናም በልባቸው ትሁት እንዲሆኑ አስተምራቸው፤ ማንኛውንም የዲያብሎስ ፈተና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ባላቸው እምነት እንዲቋቋሙ አስተምራቸው።

፴፬ ለመልካም ስራ በጭራሽ እንዳይታክቱ፣ ነገር ግን የዋህ፣ እናም በልባቸው ትሁት እንዲሆኑ አስተምራቸው፤ ምክንያቱም እንደ እነዚህ ያሉት ለነፍሳቸው ዕረፍትን ያገኛሉና።

፴፭ ልጄ ሆይ፣ አስታውስ፣ እናም በጎልማሳነትህ ዘመን ጥበብን ተማር፤ አዎን፣ በወጣትነትህ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት መጠበቅን ተማር።

፴፮ አዎን፣ እናም ለድጋፍህ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጩህ፤ አዎን፣ ስራህ ሁሉ ለጌታ ይሁን፣ እናም ወደ የትኛውም ሥፍራ ብትሄድ በጌታ ይሁን፤ አዎን፣ ሀሳብህ ሁሉ በጌታ የተመራ ይሁን፤ አዎን የልብህ ዝንባሌ ለዘለዓለም በጌታ ላይ ይሁን።

፴፯ በስራዎችህ ሁሉ ከጌታ ጋር ተማከር፣ እናም ለአንተ ጥቅም ይመራሃልና፤ አዎን፣ በምሽት በምትተኛበት ጊዜ በእንቅልፍህ ይጠብቅህ ዘንድ በጌታ ተኛ፤ እናም ጠዋት ከመኝታህ በምትነቃበት ጊዜ ልብህ ሁሉ እግዚአብሔርን በማመስገን ይሞላ፤ እናም እነዚህን ነገሮች የምታደርግ ከሆነ፣ በመጨረሻው ቀን ከፍ ትደረጋለህ።

፴፰ እናም አሁን ልጄ፣ አባቶቻችን ኳስ ወይንም ጠቋሚ ብለው ስለሚጠሩት፣ ወይም በትርጉም አቅጣጫን የሚጠቁም መሳሪያ የሆነው፣ አባቶቻችን ሊያሆና ብለው የሚጠሩትን በሚመለከት በመጠኑ የምናገረው አለኝ፤ እናም እርሱንም ጌታ አዘጋጅቶታል።

፴፱ እናም እነሆ፣ እንደዚህ አይነት አስደናቂ የእጅ ስራን ሊሰራ የሚችል ማንም ሰው የለም። እናም እነሆ፣ አባቶቻችን በምድረበዳው ውስጥ እንዲጓዙበት አቅጣጫን ለማሳየት ተዘጋጅቶ ነበር።

እናም ይህም ይሰራ የነበረው በእግዚአብሔር ባላቸው እምነት መሰረት ነበር፤ ስለዚህ፣ እግዚአብሔር እንዝርቱ የሚሄዱበትን አቅጣጫ እንዲያመለክት እንደሚያደርገው ለማመን እምነት በነበራቸው መጠን፣ እነሆ ተከናውኖላቸዋል፤ ስለዚህ ይህ ተአምራት ነበራቸው፣ እናም ደግሞ ብዙ ከቀን ቀን በእግዚአብሔር ኃይል የነበሩ ሌሎች ታምራቶች ነበሯቸው።

፵፩ ይሁን እንጂ፣ እነዚያ ታምራቶች በትንሽ ነገር የተደረጉ ቢሆንም ድንቅ ስራዎችን አሳይተዋቸው ነበር። እነርሱ ሰነፍ ነበሩ፣ እናም እምነታቸውንና ትጋታቸውን መለማመድ ረሱ፣ እናም እነዚያ ድንቅ ስራዎች ቆሙና፣ በጉዞአቸውም ወደፊት አልቀጠሉም፤

፵፪ ስለዚህ፣ በምድረበዳው ውስጥ ቆዩ፣ እንዲሁም ቀጥታውን መንገድ አልተጓዙም፣ እናም በመተላለፋቸው ምክንያት በረሃብና በጥም ተሰቃዩ።

፵፫ እናም አሁን፣ ልጄ፣ እነዚህ የነገሮች ጥላ የሌላቸው አለመሆናቸውን እንድትገነዘብ እፈልጋለሁ፤ አባቶቻችን ለዚህ አቅጣጫ ጠቋሚ መሳሪያ ትኩረትን ላለመስጠት ሰነፍ በሆኑ ጊዜ (አሁን እነዚህ ነገሮች ጊዜያዊ ነበሩ) አልበለፀጉም፤ መንፈሳዊ ለሆኑትም ነገሮች ቢሆን እንዲሁ ነው።

፵፬ እነሆም አባቶቻችንም ወደ ቃል ኪዳን ምድር በቀጥተኛው መንገድ የሚያመራቸውን ኮምፓስ መከተሉ አይነት ወደ ዘለዓለማዊው ደስታ የሚያመራ ቀጥተኛው መንገድ የሆነውን የክርስቶስን ቃል መቀበልም ነው።

፵፭ እናም አሁን እንዲህ እላለሁ፣ ለዚህ ነገር ምሳሌ የለምን? በእርግጥ ይህ አመልካች ጎዳናውን ተከትሎ አባቶቻችንን ወደ ቃል ኪዳኑ ምድር እንዳመጣ፣ የክርስቶስንም ቃላት ከተከተልናቸው ከዚህ ከሀዘን ሸለቆ እጅግ ወደ ተሻለው የቃል ኪዳን ምድር ይወስደናል።

፵፮ ልጄ ሆይ፣ መንገዱ ቀላል በመሆኑ ሰነፍ አንሁን፤ ለአባቶቻችንም እንዲሁ ነበርና፣ ለእነርሱም የሚመለከቱት ከሆነ በህይወት ይቆዩ ዘንድ ለዚህ ተዘጋጅቶላቸው ነበርና፤ ለእኛም ቢሆን እንዲሁ ነው። መንገዱ ተዘጋጅቷል፣ እናም የምንመለከት ከሆነ ለዘለዓለም እንኖራለን።

፵፯ እናም አሁን፣ ልጄ፣ እነዚህን ቅዱስ ነገሮች ጠብቅ፤ አዎን፣ ወደ እግዚአብሔር ተመልከትና ኑር። ወደዚህ ህዝብ ሂድና፣ ቃሉን ተናገር፣ እናም ንቃ። ልጄ ደህና ሰንብት።