ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፳፯


ምዕራፍ ፳፯

ጌታ አሞንን የአንቲ-ኔፊ-ሌሂዎች ሰዎች በደህንነት ወደሚቀመጡበት ቦታ እንዲመራቸው አዘዘው—አልማን ባገኘው ጊዜ የአሞን ደስታ አቅም አሳጣው—ኔፋውያን ለአንቲ-ኔፊ-ሌሂዎች የኢየርሾንን ምድር ሰጡአቸው—እነርሱም የአሞን ህዝብ ተብለው ተጠሩ። ከ፺–፸፯ ም.ዓ. ገደማ።

እንግዲህ እንዲህ ሆነ ከኔፋውያን ጋር ለጦርነት የሄዱት እነዚያ ላማናውያን፣ እነርሱን ለማጥፋት ብዙ ከታገሉ በኋላ፣ ጥፋታቸውን መሻት ከንቱ ሆኖ ባገኙት ጊዜ፣ በድጋሚም ወደኔፊ ምድር ተመለሱ።

እናም እንዲህ ሆነ አማሌቂውያን፣ በደረሰባቸው ሽንፈት ምክንያት እጅግ ተቆጡ። እናም ኔፋውያንን ለመበቀል እንዳልቻሉ በተመለከቱ ጊዜ፣ በወንድሞቻቸው በአንቲ- ኔፊ-ሌሂ ህዝቦች ላይ ሰዎችን በቁጣ ማነሳሳት ጀመሩ፤ ስለዚህ በድጋሚ እነርሱን ማጥፋት ጀመሩ።

እንግዲህ እነኚህ ህዝቦች በድጋሚ መሳሪያዎቻቸውን ለማንሳት እምቢተኞች ሆኑ፣ እናም በጠላቶቻቸው ፍላጎት መሠረት ለመሞት ፈቃደኞች ሆኑ።

እንግዲህ አሞንና ወንድሞቹ በተወደዱባቸው እናም እጅግ በወደዱአቸው መካከል ይህን የጥፋት ስራ በተመለከቱ ጊዜ—ከዘለዓለማዊው ጥፋት እነርሱን ለማዳን እንደመልአክ ከእግዚአብሔር እንደተላኩ ተመስለዋልና—ስለዚህ፣ አሞንና ወንድሞቹ ይህን ታላቅ ጥፋት በተመለከቱ ጊዜ፣ እጅግ አዘኑ፣ እናም ለንጉሱ እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፥

እነኚህን የጌታ የሆኑትን ሰዎች በአንድ ላይ እንሰብስባቸው፣ እናም ወደ ኔፋውያን ወንድሞቻችን ወደ ዛራሔምላ ምድር እንውረድና፣ እንዳንጠፋ ከጠላቶቻችን እጅ እናምልጥ።

ነገር ግን ንጉሱ እንዲህ አላቸው፥ እነሆ፣ ብዙ ግድያዎችንና ኃጢያቶችን በእነርሱ ላይ በመፈፀማችን ኔፋውያን ያጠፉናል።

እናም አሞን እንዲህ አለ፥ እሄዳለሁና፣ ጌታን እጠይቀዋለሁ፣ እናም እርሱ ወደ ወንድሞቻችን ሂዱ ቢለን፣ ትሄዳላችሁን?

እናም ንጉሱ እንዲህ አለው፥ አዎን፣ ጌታ ሂዱ ብሎ ከተናገረን፣ ወደ ወንድሞቻችን እንሄዳለን፣ እናም በእነርሱ ላይ የፈፀምናቸውን ግድያዎችና ኃጢአቶች እስክንክስ አገልጋዮቻቸው እንሆናለን።

ነገር ግን አሞን እንዲህ አለው፥ በወንድሞቼ መካከል ማንንም በባርነት መያዝ በአባቴ ከተመሰረተው ህግ ላይ ተቃራኒ ነው፤ ስለዚህ እንሂድ እናም በወንድሞቻችን ምህረት ላይ እንመካ።

ነገር ግን ንጉሱ እንዲህ አለው፥ ጌታን ጠይቅ፣ እናም እርሱ ሂዱ ካለን እንሄዳለን፤ አለበለዚያ በምድሪቱ እንጠፋለን።

፲፩ እናም እንዲህ ሆነ አሞን ሄደና ጌታን ጠየቀ፣ ጌታም እንዲህ አለው፥

፲፪ ይህ ህዝብ እንዳይጠፋ ከዚህ ምድር አስወጣቸው፣ ምክንያቱም ላማናውያን ወንድሞቻቸውን ለመግደል በሚያውኩ አማሌቂውያን ልብ ሰይጣን በሀይል ይዞታልና፤ ስለዚህ ከዚህ ምድር ውጣ፤ እናም በዚህ ትውልድ ያለ ህዝብ የተባረከ ነው፣ እጠብቀዋለሁና።

፲፫ እናም አሁን እንዲህ ሆነ አሞን ጌታ የተናገረውን ቃል ሁሉ ሄዶ ለንጉሱ ተናገረ።

፲፬ እናም ህዝቦቻቸውን በአንድ ላይ ሰበሰቡ፤ አዎን፣ የጌታ የሆኑትን ሰዎች በሙሉ፣ እናም ከብቶቻቸውንና መንጋዎቻቸውን በሙሉ በአንድ ላይ ሰበሰቡ፣ እናም ከምድሪቱ ወጥተው ሄዱና፣ የኔፊን ምድር ከዛራሔምላ ምድር ወደሚከፍለው ምድረበዳ ደረሱ፣ ወደ ምድሪቱ ዳርቻ አጠገብም ደረሱ።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ አሞን እንዲህ አላቸው፥ እነሆ፣ እኔና ወንድሞቼ ወደ ዛራሔምላ ምድር እንሄዳለን፣ እናንተም እኛ እስከምንመለስ ድረስ እዚህ ትቆያላችሁ፤ እናም በምድራቸው እንድትመጡ እንዲፈቅዱ የልብ ፍላጎታቸውን ለማወቅ እንሞክራለን።

፲፮ እናም እንዲህ ሆነ አሞን ወደ ምድሪቱ በሄደ ጊዜ፣ እርሱና ወንድሞቹ በተነገረው ቦታ አልማን አገኙት፤ እናም እነሆ፣ ይህም አስደሳች ግንኙነት ነበር።

፲፯ እንግዲህ የአሞን ደስታ ሙሉ እስኪሆን ታላቅ ነበር፤ አዎን፣ በአምላኩም ደስታ ተውጦ ነበር፤ ጉልበቱ እንኳን እስከሚደክም ድረስ፤ እናም በድጋሚ በመሬት ላይ ወደቀ።

፲፰ እንግዲህ ይህ ታላቅ ደስታ አይደለምን? እነሆ እውነተኛ ንስሀ ገቢ እና ትሁት ደስታን ፈላጊ ካልሆነ በቀር ማንም የማይቀበለው ደስታ ነው።

፲፱ እንግዲህ አልማ ወንድሞቹን በማግኘቱ ደስታው በእውነት ታላቅ ነበር፤ እናም ደግሞ የአሮን፣ ኦምነርና፣ የሄምኒ ደስታ ታላቅ ነበር፤ ነገር ግን እነሆ ደስታቸው ከጉልበታቸው በላይ አልነበረም።

እናም እንዲህ ሆነ አልማ ወንድሞቹን ወደ ዛራሔምላ ምድር፣ እንዲሁም ወደራሱ ቤትም፣ በመምራት መለሳቸው። እናም ሄዱና፣ በወንድሞቻቸው በላማናውያን መካከል በኔፊ ምድር የሆኑትን ነገሮች ለዋናው ዳኛ ተናገሩ።

፳፩ እናም እንዲህ ሆነ ዋናው ዳኛ የአንቲ-ኔፊ-ሌሂዎች ሰዎች የሆኑትን በምድሪቱ ይገቡ ዘንድ በሚመለከት የህዝብን ድምፅ ለመፈለግ በምድሪቱ ሁሉ አዋጅ ላከ።

፳፪ እናም እንዲህ ሆነ የህዝቡ ድምፅ እንዲህ በማለት መጣ፥ እነሆ፣ በባህሩ በስተምስራቅ በኩል ያለው ለጋስን ምድር የሚያገናኘውን፣ በለጋስም ምድር በስተደቡብ ያለው የኢየርሾንን ምድር እንተዋለን፤ እናም ይህ የኢየርሾን ምድር እንዲወርሱት ለወንድሞቻችን የምንሰጠው ምድር ነው።

፳፫ እናም እነሆ፣ በኢየርሾን ምድር ወንድሞቻችንን እንጠብቃቸው ዘንድ በኢየርሾንና በኔፊ ምድር መካከል ወታደሮቻችንን እናስቀምጣለን፤ እናም ይህን ለወንድሞቻችን የምናደርገው በወንድሞቻቸውም ላይ መሳሪያዎቻቸውን በማንሳት ኃጢያት እንዳይፈፅሙ ባላቸው ፍርሀት ምክንያት ነው፤ እናም ይህ ታላቅ ፍርሃት የመጣው ለበርካታ ግድያዎቻቸውና አሰቃቂ ኃጢአታቸው ከገቡት መሪር ንስሃ የተነሳ ነው።

፳፬ እናም አሁን እነሆ፣ የኢየርሾንን ምድር ይወርሱ ዘንድ ይህንን ለወንድሞቻችን እናደርጋለን፤ እናም ወታደሮቻችንን ለማቆየት የምንረዳበት ነገር የሚሰጡን ከሆነ በወታደሮቻችን ከጠላቶቻቸው እንጠብቃቸዋለን።

፳፭ እናም እንዲህ ሆነ አሞን ይህንን በሰማ ጊዜ፣ ወደ አንቲ-ኔፊ-ሌሂዎች ሰዎች ተመለሰ፣ ደግሞም አልማ ከእርሱ ጋር ድንኳናቸውን በተከሉበት ምድረበዳ ተመለሱና፣ ይህንን ነገር ሁሉ እንዲያውቁ አደረጉአቸው። እናም አልማ ከአሞንና፣ ከአሮን እንዲሁም ከወንድሞቹ ጋር የእርሱን መለወጥ ተረከላቸው።

፳፮ እናም እንዲህ ሆነ ይህ ነገርም በመካከላቸው የታላቅ ደስታ መንስኤ ነበር። እናም ወደ ኢየርሾን ምድር ሄዱና፣ የኢየርሾን ምድርን በባለቤትነት ወሰዱ፤ እናም በኔፋውያን የአሞን ህዝብ ተብለው ተጠሩ፤ ስለዚህ ከዚያን ጊዜም በኋላ በዚህ ስም ተለይተው ይታወቃሉ።

፳፯ እናም እነርሱ ከኔፊ ህዝብ ጋር ነበሩ፣ ደግሞም የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ከነበሩት ሰዎች ጋር ተቆጠሩ። እናም ለእግዚአብሔርና፣ ደግሞ ለሰዎች ባላቸው ቅንአት ይለዩ ነበር፤ ምክንያቱም በሁሉም ነገር ፍፁም ታማኝና ቀጥተኞች ነበሩ፤ እናም እስከመጨረሻ በክርስቶስ እምነት ፅኑ ነበሩ።

፳፰ እናም የወንድሞቻቸውን ደም ማፍሰስን በታላቅ ጥላቻ ተመለከቱ፤ በወንድሞቻቸው ላይ መሣሪያን ለማንሳትም በጭራሽ ሊገፋፉ አይቻሉም፤ እናም በክርስቶስና በትንሳኤው ባላቸው ተስፋና ግንዛቤ፣ ሞትን በፍርሃት ደረጃ በጭራሽ አልተመለከቱም፤ ስለዚህ ሞታቸው በክርስቶስ ሞት ድል ተነስቷል።

፳፱ ስለዚህ ወንድሞቻቸውን ለመምታት ጎራዴውን እንዲሁም ሻቡላውን ከመውሰዳቸው በፊት በወንድሞቻቸው ሊደርስባቸው በሚችል እጅግ በሚያሰቅቅና በሚያሰቃይ ሁኔታ ሞትን ይቀበላሉ።

እናም እነርሱ ቅንዓት ያላቸውና የተወደዱ ሰዎች፣ በጌታም እጅግ የተወደዱ ሰዎች ነበሩ።