ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፳፪


ምዕራፍ ፳፪

አሮን ስለፍጥረት፣ ስለአዳም መውደቅ፣ በክርስቶስም ስላለው የቤዛነት ዕቅድ የላሞኒን አባት አስተማረ—ንጉሱ እና ቤተሰቦቹ በሙሉ ተለወጡ—በኔፋውያንና በላማናውያን መካከል የመሬት ክፍፍሉ ተገልጿል። ከ፺–፸፯ ም.ዓ. ገደማ።

እንግዲህ አሞን ያለማቋረጥ የላሞኒን ሰዎች በማስተማር ላይ እያለ፣ ወደ አሮን እና ወንድሞቹ ታሪክ እንመለሳለን፤ እርሱ ከሚዶኒ ወጥቶ ከሄደ በኋላ በመንፈስ ወደኔፊ ምድር፣ እንዲሁም ከእስማኤል ምድር በስተቀር በምድሪቱ ላይ ሁሉ ንጉሥ ወደ ሆነውም ቤት እንኳን ተመርቷል፤ እናም እርሱም የላሞኒ አባት ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ አሮን ከወንድሞቹ ጋር ወደ ንጉሱ ቤተመንግስት ሄደና፣ ከንጉሱ ፊት ሰገደ፣ እናም እንዲህ አለው፥ እነሆ፣ ንጉስ ሆይ፣ አንተ ከወህኒ ቤት የለቀቅኸን፣ የአሞን ወንድሞች ነን።

እናም አሁን፣ ንጉስ ሆይ፣ ነፍሳችንን የምታተርፍ ከሆነ፣ አገልጋዮችህ እንሆናለን። እናም ንጉሱ እንዲህ አላቸው፥ ተነሱ ህይወታችሁን እሰጣችኋለሁ፣ አገልጋዮቼ እንድትሆኑም አልፈቅድም፤ ነገር ግን እንድትሰብኩልኝ እጠይቃችኋለሁ፤ ምክንያቱም በጥቂቱም እንኳን ቢሆን በወንድማችሁ አሞን ደግነትና በቃሉ ታላቅነት አዕምሮዬ ታውኳልና፤ እናም እርሱ ከሚዶኒ ወጥቶ ከእናንተ ጋር ለምን እንዳልመጣም ምክንያቱን ለማወቅ እፈልጋለሁ።

እናም አሮን ለንጉሱ እንዲህ አለው፥ እነሆ የጌታ መንፈስ ወደሌላ ቦታ እንዲሄድ ጠርቶታል፤ እርሱም የላሞኒን ህዝብ ለማስተማር ወደ እስማኤል ምድር ሄዷል።

አሁን ንጉሱ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥ ስለጌታ መንፈስ የተናገራችሁት ይህ ምንድን ነው? እነሆ እኔን የሚያውከኝ ነገር ይህ ነው።

እናም ደግሞ አሞን—ንስሃ የምትገቡ ከሆነ ትድናላችሁ፣ እናም ንስሃ ካልገባችሁ በመጨረሻው ቀን ትጣላላችሁ በማለት የተናገረው ይህ ምንድን ነው?

እናም አሮንም መለሰለትና፣ እንዲህ ሲል ተናገረው፥ እግዚአብሔር መኖሩን ታምናለህን? እናም ንጉሱም እንዲህ አለ፥ አማሌቂውያን እግዚአብሔር አለ እንደሚሉ አውቃለሁ፣ እርሱን ለማምለክ እራሳቸውን በአንድነት ይሰበስቡ ዘንድ ቅዱስ ሥፍራን እንዲሰሩ ፈቃድ ሰጥቻቸዋለሁም። እናም አንተ አሁን እግዚአብሔር አለ የምትል ከሆነ እነሆ እኔ አምናለሁ

እናም አሁን አሮን ይህን በሰማ ጊዜ ልቡ ሃሴት ማድረግ ጀመረች፣ እናም እንዲህ አለ፥ እነሆ አንተ ህያው እንደሆንክ፣ ንጉስ ሆይ፣ እግዚአብሔርም አለ።

እናም ንጉሱም እንዲህ አለ፥ አባቶቻችንን ከኢየሩሳሌም ምድር ያወጣው ያ ታላቁ መንፈስ እግዚአብሔር ነውን?

እናም አሮን እንዲህ አለው፥ አዎን እርሱ ያ ታላቁ መንፈስ ነው፣ እናም በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ ፈጥሯል። ይህንን ታምናለህን?

፲፩ እናም እንዲህ አለ፥ አዎን ታላቁ መንፈስ ሁሉን ነገሮች እንደፈጠረ አምናለሁ፣ እነዚህን ሁሉ በተመለከተ እንድትነግረኝም እፈልጋለሁ፣ እናም ቃልህን አምናለሁ።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ አሮን ንጉሡ ቃሉን እንደሚያምነው በተመለከተ ጊዜ፣ ከአዳም መፈጠር ጀምሮ ያሉትን ከቅዱሳት መጻሕፍት ለንጉሡ ያነብለት ጀመረ—እግዚአብሔር ሰውን በአምሳሉ እንዴት እንደፈጠረ፣ እናም እግዚአብሔርስ እንዴት ትዕዛዛትን እንደሰጠው፣ እናም በመተላለፉ የተነሳም ሰው እንደወደቀ አነበበ።

፲፫ እናም አሮን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከአዳም መፈጠር ጀምሮ፣ የሰዎችን መውደቅ በፊቱ በማኖር፣ በስጋ ያሉበትን ሁኔታ፣ እናም ደግሞ ከዓለም መፈጠር ጀምሮ፣ በክርስቶስ በኩል፣ በስሙ ለሚያምኑ ሁሉ የተዘጋጀውን የቤዛነት ዕቅድ አስረዳው።

፲፬ እናም ሰው በመውደቁ የተነሳ ስለራሱ በማንኛውም ነገር ብቁ ለመሆን አይችልም፤ ነገር ግን የክርስቶስ ስቃዩና ሞቱ በእምነታቸውና በንስሃቸውና በሚመሳሰሉት አማካይነት ለኃጢአታቸው ክፍያ ይሆናል፣ እናም እርሱም የሞትን እስራት በጣጥሷል፤ ሞትም ድል አይኖረውም፣ እናም የሞት መውጊያ በክብር ተስፋ ይዋጣል፤ እናም አሮን እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለንጉሱ አስረዳ።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ አሮን እነዚህን ነገሮች በሙሉ ለንጉሱ ካስረዳው በኋላ፣ ንጉሱ እንዲህ ሲል ተናገረ፥ አንተ የተናገርከውን ይህን ዘለዓለማዊ ህይወት እንዳገኝ ምን ማድረግ አለብኝ? አዎን፣ ከእግዚአብሔር እንድወለድ፣ እናም ይህ እርኩስ መንፈስ ከደረቴ እንዲነቀልና፣ መንፈሱን ተቀብዬ በደስታ እሞላ ዘንድ፣ በመጨረሻው ቀንም እንዳልጣል፣ ምን ማድረግ አለብኝ? እነሆ፣ ያለኝን ሁሉ እተዋለሁ፣ አዎን ይህን ታላቁን ደስታም እቀበል ዘንድ መንግስቴን እለቃለሁ።

፲፮ ነገር ግን አሮን እንዲህ አለው፥ ይህንን ነገር ከፈለግህ፣ በእግዚአብሔር ፊት ከሰገድህ፣ አዎን፣ ለኃጢያትህ ሁሉ ንስሃ ከገባህና፣ በእግዚአብሔር ፊት ከሰገድህ፣ እናም እንደምትቀበል በማመን ስሙን በእምነት ከጠራህ የፈለከውን ተስፋ ታገኛለህ።

፲፯ እናም እንዲህ ሆነ አሮን እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፣ ንጉሱ በጉልበቱ ተንበርክኮ በጌታ ፊት ሰገደ፣ አዎን፣ በመሬትም ላይ እራሱን ዘረጋ፣ እናም እንዲህ በማለት በኃይል ጮኸ

፲፰ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፣ አሮን እግዚአብሔር እንዳለ ነግሮኛል፤ እናም እግዚአብሔር ካለና፣ አንተ እግዚአብሔር ከሆንክ፣ አንተንም እንዳውቅ ታደርጋለህን፣ እናም ከሞት እነሳ ዘንድና፣ በመጨረሻው ቀን እድን ዘንድ፣ አንተን ለማወቅ ኃጢአቴን በሙሉ እተዋለሁ። እናም እንግዲህ ንጉሱ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፣ እንደሞተ አይነት ወደቀ።

፲፱ እናም እንዲህ ሆነ አገልጋዮቹ ሮጡና፣ በንጉሱ ላይ የሆነውን ሁሉ ለንግስቲቱ ነገሯት። እናም እርሷ ወደንጉሱ መጣች፤ እንደሞተ መውደቁን ባየችም ጊዜና፣ ደግሞ አሮንና ወንድሞቹ ለመውደቁ እንደምክንያት በመሆን መቆማቸውን በተመለከተች ጊዜ፣ በእነርሱ ተቆጣች፣ እናም አገልጋዮችዋ፣ ወይም የንጉሱ አገልጋዮች፣ እነርሱን ወስደው እንዲገድሉአቸው አዘዘች።

አሁን አገልጋዮቹ ንጉሱ የወደቀበትን መንስኤ ያውቃሉ፣ ስለዚህ በአሮንና በወንድሞቹ ላይ እጃቸውን ለመጫን አልደፈሩም፤ እናም ንግስቲቱን እንዲህ በማለት ተማፀኗት፥ እነሆ ከእነዚህ አንዱ ከሁላችንም በላይ ኃያል የሆኑትን ሰዎች እንድንገድል ለምን ታዢናለሽ? ስለሆነም በፊታቸው እንወድቃለን።

፳፩ እንግዲህ ንግስቲቱ የአገልጋዮቹን ፍርሃት በተመለከተች ጊዜ በእርሷም ላይ ክፉ የሆነ ነገር እንዳይመጣባት እጅግ መፍራት ጀመረች። እናም አገልጋዮቿ አሮንና ወንድሞቹን እንዲገድሉ ህዝቦችን እንዲጠሩ አዘዘች።

፳፪ እንግዲህ አሮን የንግስቲቱን ፅኑ ውሳኔ በተመለከተ ጊዜ፣ የህዝቡንም ልበ ጠጣርነት የሚያውቅ በመሆኑ፣ ብዙዎች እራሳቸውን በአንድነት ከሰበሰቡ፣ እናም ታላቅ ፀብና ረብሻ በመካከላቸው ይኖራል ብሎም ፈራ፤ ስለዚህ አሮን እጁን አንስቶ ንጉሱን ከመሬት አነሳውና፣ እንዲህ አለው፥ ቁም። እናም ብርታትን አግኝቶ በእግሩ ቆመ።

፳፫ እንግዲህ ይህ የተደረገው በንግሥቲቱና በብዙዎቹ አገልጋዮች ፊት ነበር። እናም ይህንንም በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ተገረሙና መፍራት ጀመሩ። እናም ንጉሱ ተነሳን፣ ይሰብክላቸው ጀመር። ለእነርሱም ሰበከና፣ እንዲህም ሆኖ ቤተሰቦቹ በሙሉ ወደጌታ ተለወጡ

፳፬ እንግዲህ በንግስቲቱ ትዕዛዝ መሰረት ብዙዎች በአንድነት ተሰብስበው ነበር፣ እናም በአሮንና ወንድሞቹም የተነሳ በመካከላቸው ብዙዎች ማጉረምረም ጀምረው ነበር።

፳፭ ነገር ግን ንጉሱ በመካከላቸው ቆመና፣ አገለገላቸው። እናም በአሮንና ከእርሱ ጋር በነበሩት መረጋጋትን አገኙ።

፳፮ እናም እንዲህ ሆነ ንጉሱ የህዝቡን መረጋጋት በተመለከተ ጊዜ፣ አሮንና ወንድሞቹ በህዝቡ መካከል እንዲቆሙና ቃሉን እንዲሰብኩ አደረገ።

፳፯ እናም እንዲህ ሆነ ንጉሱ በምድሪቱ ሁሉ ባሉት ሰዎች መካከል፣ በዙሪያውም ባለው ክልል በባህሩም ዳርቻ፣ በምስራቅና በስተምዕራብ፣ ከዛራሔምላ ምድር በምድረበዳው ከምስራቁ ባህር ጀምሮ እስከምዕራብ በሚከፍለው በቀጭኑ መንገድ፣ እናም በባህሩም ዳርቻና በምድረበዳው ዳርቻ፣ በዛራሔምላ በስተሰሜን በኩል በማንቲ ዳርቻ በሲዶም ወንዝ ምንጭ በኩል፣ ከምስራቅ ወደምዕራብ በሚፈሰው በኩል አዋጅ ላከ—እናም ይህም ላማናውያንና ኔፋውያን የተከፈሉበት ነው።

፳፰ እንግዲህ፣ ብዙዎቹ የላማናውያን ስራ ፈቶች በምድረበዳው ውስጥ ኖሩ፣ እናም በድንኳን ኖሩ፤ በኔፊ ምድር ውስጥ በስተምዕራብ ምድረበዳው በኩልም ተዘረጉ፤ አዎን፣ እናም ደግሞ በዛራሔምላ ምድር በስተምዕራብ በኩል፣ በባህሩ ዳርቻና፣ በኔፊ ምድር በስተምዕራብ በመጀመሪያው የአባቶቻቸው የርስት ሥፍራ እናም በባህሩ ዳርቻ ነበሩ።

፳፱ እናም ደግሞ ኔፋውያን ካባረሩአቸው አካባቢ በባህሩ ዳርቻ በስተምስራቅ በኩል ብዙ ላማናውያን ነበሩ። እናም በዚያም ኔፋውያን ሙሉ በሙሉ በላማናውያን ሊከበቡ ተቃርበው ነበር፤ ይሁን እንጂ ኔፋውያን በምድረበዳው ወሰን በስተሰሜን በኩል፣ በሲዶም ወንዝ መነሻ፣ ከምስራቅ እስከምዕራብ፣ በምድረበዳው ዙሪያ ያሉትን ሥፍራዎች ተቆጣጥረዋል፣ በስተሰሜን በኩል፣ ለጋስ ብለው በሚጠሩት ምድር እስከሚመጡም ድረስ እንኳን ተቆጣጥረዋል።

እናም ይህም ወደ ሰሜን የሚርቅ ሆኖ፣ የዛራሔምላ ህዝቦች በመጀመሪያ ያረፉበት ስፍራ በመሆኑ ያገኙበት ስለአጥንታቸው የተናገርንባቸው ሰዎች ኖረውበት እናም ተደምስሰውበት ወደነበረው ምድር ውስጥ እየገባ፣ የወደመ ስፍራ ብለው የሚጠሩትን ያዋስን ነበር።

፴፩ እናም እነርሱም በምድረበዳው በስተደቡብ በኩል መጡ። በስተሰሜን በኩል ያለው ቦታም የወደመው ስፍራ ተብሎ ይጠራ ነበር፣ እናም በስተደቡብ በኩል ያለው ምድር ለጋስ ተብሎ ይጠራል፣ ይህም በተለያዩ የዱር አውሬዎች ተሞልቶ የነበረ፣ ከፊሎቹም ምግብ ፍለጋ ከሰሜን በኩል የመጡ ነበሩበት፣ ምድረበዳው ነበር።

፴፪ እናም አሁን፣ ለኔፋውያን እስከ ለጋሱ ምድርና እስከ ወደመው ስፍራ ከባህሩ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ርቀቱም የአንድ ቀን ተኩል ጉዞ ብቻ ነበር፤ እናም የኔፊና የዛራሔምላ ምድር ከሞላ ጎደል በውሃ የተከበበ ነበር፤ በስተሰሜንና በስተደቡብ ምድር መካከል ቀጭን ሥፍራ ነበር።

፴፫ እናም እንዲህ ሆነ ኔፋውያን ለጋስን ምድር፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራቡ ባህር፣ ይኖሩበት ነበር፤ እናም ኔፋውያን ላማናውያን በስተሰሜን ምንም ሀብት እንዳይኖራቸው፣ በስተሰሜንም ያለውን ሥፍራ እንዳያጥለቀልቁት በብልሃታቸው ከጠባቂዎቻቸውና ከወታደሮቻቸው ጋር በስተደቡብ ባለው ሥፍራ አገዱአቸው።

፴፬ ስለዚህ በኔፊ ምድር እና በዙሪያው ካለው ምድረበዳ በስተቀር ላማናይቶች ምንም ይዞታዎች ሊኖሯቸው አልቻሉም። ላማናውያን ለእነርሱ ጠላት በመሆናቸው፣ በየትኛውም አቅጣጫ አንዳያሰቃዩአቸው፣ እናም ደግሞ እንደፍላጎታቸው የሚሸሹበትን ሃገር ያገኙ ዘንድ እንግዲህ በኔፋውያን ይህ ብልህነት ነው።

፴፭ እናም አሁን እኔ፣ ይህን ካልኩኝ በኋላ፣ ወደ አሞንና አሮን፣ ኦምነርና ሂምኒ፣ እናም ወንድሞቻቸው ታሪክ በድጋሚ እመለሳለሁ።