ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፳፩


አሮንና፣ ሙሎቄ፣ እና ወንድሞቻቸው ለላማናውያን የሰበኩበት ታሪክ።

ከምዕራፍ ፳፩ እስከ ፳፮ አጠቃሎ የያዘ።

ምዕራፍ ፳፩

አሮን አማሌቂውያንን ስለክርስቶስና ስለኃጢያት ክፍያው አስተማረ—አሮንና ወንድሞቹ በሚዶኒ ታሰሩ—ከዳኑ በኋላ፣ በምኩራቦች አስተማሩ፣ እናም ብዙዎችን ለወጡ—ላሞኒ በእስማኤል ምድር ለሚኖሩ ህዝቦች የኃይማኖት ነፃነትን ሰጣቸው። ከ፺–፸፯ ም.ዓ. ገደማ።

እንግዲህ አሞንና ወንድሞቹ በላማናውያን ምድር ዳርቻ በተለያዩ ጊዜ፣ እነሆ አሮን በላማናውያን ኢየሩሳሌም ተብላ ወደ ምትጠራበት፣ እንደ አባቶቻቸው የትውልድ ሥፍራ ስም ወደተጠራችው ስፍራ ጉዞውን አደረገ፤ እናም ስፍራውም ራቅ ያለና በሞርሞን ዳርቻ ነበር።

ላማናውያንና አማሌቂውያን፣ እናም የአሙሎን ሰዎች፣ ኢየሩሳሌም በመባል የታወቀች ታላቅ ከተማን ገንብተው ነበር።

እንግዲህ ላማናውያን እጅግ ጠጣር ነበሩ፤ ነገር ግን አማሌቂውያን እናም አሙሎናውያን ይበልጥ ጠጣሮች ነበሩ፣ ስለዚህ ላማናውያንም ልባቸውን እንዲያጠጥሩ፣ በክፋታቸውና በእርኩሰታቸውም እንዲጠናከሩ አደረጉአቸው።

እናም እንዲህ ሆነ አሮን ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መጣ፣ እናም በመጀመሪያ ለአማሌቂውያን መስበክ ጀመረ። እናም በምኩራባቸው መስበክ ጀመረ፣ ምክንያቱም እንደኔሆራውያን አሠራር ምኩራብ ሰርተዋልና፤ ብዙ አማሌቂውያንና አሙሎናውያን የኔሆርን ስርዓት የሚከተሉ ነበሩና።

ስለዚህ፣ አሮን በአንደኛው ምኩራብ ህዝቡን ለማስተማር በገባ ጊዜ፣ እናም ለእነርሱ በሚናገር ጊዜ፣ እነሆ አንድ አሙሌቃዊ ተነሳና፣ ከእርሱም ጋር እንዲህ በማለት መጣላት ጀመረ፥ አንተ የመሰከርከው ያ ምንድነው? መልአክን ተመልክተሃልን? መላዕክት ለምን ለእኛ አይገለጡልንም? እነሆ እነዚህ ሰዎች እንደ አንተ ሰዎች መልካም አይደሉምን?

ደግሞም ንስሃ ካልገባን እንጠፋለን ብለሃል። የልባችንን ሃሳብና መሻት እንዴት አወቅህ? ንሰሃ ለመግባት ምክንያት እንዳለን እንዴት አወቃችሁ? የጽድቅ ሰዎች አለመሆናችንንስ እንዴት አወቃችሁ? እነሆ ቅዱሳን ስፍራዎችን ሰርተናል፣ እናም እግዚአብሔርን ለማምለክ እራሳችንን በአንድ ላይ እንሰበስባለን። ጌታ ሰዎችን ሁሉ እንደሚያድን እናምናለንና።

አሁን አሮንም እንዲህ አለው፥ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጆችን ከኃጢአታቸው ለማዳን እንደሚመጣ ታምናለህን?

እናም ሰውየው አለው፥ እንደዚህ ያለ ምንም ነገር ታውቃለህ ብለን አናምንም። በእነዚህ የሞኝ ባህሎች አናምንም። ወደፊት ስለሚመጡ ነገሮች እንደምታውቅ አናምንም፣ አባቶችህ እናም ደግሞ አባቶቻችን ይመጣሉ ብለው የተናገሯቸውን በተመለከተ ያውቃሉ ብለን አናምንም።

አሁን አሮን የክርስቶስን መምጣት በተመለከተ እናም ደግሞ የሙታንን ትንሳኤ በተመለከተና በክርስቶስ ሞት፣ እና ስቃይና በደሙ የኃጢያት ክፍያ ካልሆነ በቀር ለሰው ዘር ምንም ቤዛ እንደማይኖር ለማስረዳት ቅዱሳት መጻሕፍትን ገለጠላቸው።

እናም እንዲህ ሆነ እነዚህን ነገሮች ማብራራት በጀመረ ጊዜ፣ በእርሱ ተቆጥተው ነበር፣ ያሾፉበትም ጀመሩ፤ እናም የተናገራቸውን ቃላት ለመስማት አልፈለጉም።

፲፩ ስለዚህ፣ የሚናገረውን መስማት አለመፈለጋቸውን በተመለከተ ጊዜ፣ ከምኩራባቸው ወጥቶ ሄደና፣ አኒ-አንቲ ወደምትባል መንደር ሄደ፣ እናም በዚያ ሙሎቄ ቃሉን ለእነርሱ ሲሰብክላቸው፣ ደግሞም አማንና ወንድሞቹንም አገኘ። እናም ቃሉን በተመለከተ ከብዙዎች ጋር ተከራከሩ።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ ህዝቡ ልቡን እንዳጠጠረ ተመለከቱ፣ ስለዚህ ሄዱና ወደ ሚዶኒ ምድር መጡ። እናም ለብዙዎች ቃሉን ሰበኩ፣ ያስተማሩትን ቃላት ያመኑትም ጥቂት ነበሩ።

፲፫ ይሁን እንጂ፣ አሮንና የተወሰኑ ወንድሞቹ ተወሰዱና፣ ወደ ወህኒ ቤት ተጣሉ፣ እናም ቀሪዎቹ ከሚዶኒ ምድር በዙሪያው ወዳሉ ሥፍራዎች ሸሹ።

፲፬ እናም ወደ ወህኒ ቤት የተጣሉት በብዙ ነገሮች ተሰቃይተዋል፤ እናም በላሞኒና አሞን እጅ ተለቀቁ፣ እናም በእነርሱ ምግብና ልብስ ተሰጣቸው።

፲፭ እናም ቃሉን ለማወጅ በድጋሚ ሄዱና፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወህኒ ተለቀቁ፤ እናም እንደዚህ ተሰቃይተው ነበር።

፲፮ እናም በጌታ መንፈስ በሚመሩበት በማንኛውም ቦታ በአማሌቂውያን እያንዳንዱ ምኩራብ፣ ወይም ለመግባት በሚችሉበት በማንኛውም የላማናውያን ጉባኤ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስበክ ሄዱ።

፲፯ እናም እንዲህ ሆነ ጌታ ይባርካቸው ጀመረ፣ ይህም ሆኖ ብዙዎችን እውነትን ወደ ማወቅ አመጡ፤ አዎን፣ ብዙዎችን ኃጢአታቸውንና ትክክል ያልሆነውን የአባቶቻቸውን ወግ ያስረዱአቸው ነበር።

፲፰ እናም እንዲህ ሆነ አሞንና ላሞኒ ከሚዶኒ ምድር የወርሳው ምድር ወደ ሆነው ወደ እስማኤል ምድር ተመለሱ።

፲፱ እናም ንጉስ ላሞኒ አሞን እንዲያገለግለውም ሆነ አገልጋዩ እንዲሆንም አልፈቀደም።

ነገር ግን በእስማኤል ምድር ምኩራብ እንዲሰራ አደረገ፤ እናም ህዝቡ ወይም በአገዛዙ ስር ያለው ህዝብ እራሳቸውን በአንድ ላይ እንዲሰበስቡ አደረገ።

፳፩ እናም በእነርሱ ተደሰተ፣ ብዙ ነገሮችንም አስተማራቸው። እናም ህዝቡ በእርሱ ስር እንደነበሩና፣ ነፃ ህዝብ እንደነበሩ፣ በአባቱ ከንጉሱም ጭቆና ነፃ እንደሆኑም ነገራቸው፤ ምክንያቱም አባቱ በእስማኤል ምድርና በዙሪያው ባሉት ምድር በሚኖሩት ሰዎች ላይ ይገዛ ዘንድ ሰጥቶታልና።

፳፪ እናም በንጉስ ላሞኒ አገዛዝ ስር የሆነ ምድር ከሆነ እንደፍላጎታቸው በማንኛውም ባሉበት ቦታ ጌታ አምላካቸውን ለማምለክ ነፃነት እንዳላቸውም ደግሞ አወጀላቸው።

፳፫ እናም አሞን ለንጉስ ላሞኒ ህዝብ ሰበከ፤ እናም እንዲህ ሆነ፣ ስለፅድቅ የሆኑትን ነገሮች በተመለከተ ሁሉንም ነገሮች አስተማረ። በሙሉ ትጋትም በየቀኑ መከራቸው፤ እናም ቃሉን አዳመጡትና የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ለመጠበቅ ቀናኢ ሆነው ነበር።