ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፲፰


ምዕራፍ ፲፰

ንጉስ ላሞኒ አሞን ታላቁ መንፈስ እንደሆነ ገመተ—አሞን ንጉሱን ስለፍጥረት፣ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ስላለው አድራጎትና፣ በክርስቶስ ስለሚመጣው ቤዛነት አስተማረው—ላሞኒ አመነ፣ እናም በምድሪቱ ላይ የሞተ በመምሰል ወደቀ። በ፺ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ላሞኒ አገልጋዮቹ በፊቱ እንዲቆሙና ስለሁሉም ነገሮች ድርጊቱን በተመለከተ እንዲመሰክሩ አደረገ።

እናም ሁሉም ስለተመለከቱአቸው ነገሮች ሁሉ በመሰከሩ ጊዜና፣ ንጉሱ አሞን መንጋዎቹን በመጠበቁ፣ እናም ደግሞ እርሱን ለመግደል ከፈለጉት ጋር ለመጣላት ባለው ታላቅ ኃይል ታማኝነቱን በተማረ ጊዜ፣ እጅግ ተደነቀ፣ እናም እንዲህ አለ፥ በእርግጥ ይህ ከሰው በላይ ነው። እነሆ፣ ይህ በግድያቸው የተነሳ ታላቅ ቅጣት በህዝቡ ላይ የላከው ታላቅ መንፈስ አይደለምን?

እናም ለንጉሱ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፥ እርሱ ታላቅ መንፈስም ይሁን ሰው አናውቅም፣ ነገር ግን፣ የምናውቀው ይህን ያህል ነው፣ በንጉሱ ጠላቶች መገደል አይቻልም፤ በባለሙያነቱና በታላቅ ጥንካሬው የተነሳ ከእኛም ጋር እስካለ ድረስ የንጉሱን ከብቶች ለመበታተን አይችሉም፤ ስለዚህ፣ የንጉሱ ወዳጅ መሆኑንም እናውቃለን። እናም እንግዲህ፣ ንጉስ ሆይ፣ ሰው እንደዚህ ታላቅ ኃይል ይኖረዋል ብለን አናምንም፣ ምክንያቱም እርሱ እንደማይገደል እናውቃለንና።

እናም አሁን፣ ንጉሱ እነዚህን ቃላት በሰማ ጊዜ፣ እንዲህ አላቸው፥ አሁን ይህ ታላቁ መንፈስ እንደሆነ አውቃለሁ፤ እናም በወንድሞቻችሁ እንዳደረግሁት እንዳልገድላችሁ በዚህን ጊዜ ህይወታችሁን ለማቆየት የመጣ ነው። እንግዲህ አባቶቻችን የተናገሩት ታላቁ መንፈስ ይህ ነው።

አሁን ይህ ታላቁ መንፈስ መኖሩን ላሞኒ ከአባቶቹ የተቀበለው ወግ ነው። ምንም እንኳ በታላቁ መንፈስ ያመኑ ቢሆንም፤ ያደረጉት ማንኛውም ነገር ትክክል እንደሆነ ገምተዋል፤ ይሁን እንጂ፣ አገልጋዮቹን በመግደል ስህተት እንደሰራ በመፍራት ላሞኒ በእጅጉ መፍራት ጀመረ፤

በውሃው ስፍራ ወንድሞቻቸው መንጋዎቻቸውን በማባረራቸው ብዙዎችን ገድሏልና፣ እናም ከብቶቻቸውንም ስላስበተኑ የንጉሱ አገልጋዮች ተገደሉ።

ይህም በእነርሱ መካከል የመዝረፍ ልምድ ሆኖ፣ አሁን በዚያም የተበተኑትን ወደምድራቸው ለመንዳት ይችሉ ዘንድ፣ ላማናውያን በሴቡስ ውሃ አጠገብ በመቆም የሰዎችን ከብቶች ማባረር ልምዳቸው ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ላሞኒ አገልጋዮቹን እንዲህ በማለት ጠየቃቸው፥ እንደዚህ ዓይነት ታላቅ ኃይል ያለው ሰው የት ነው?

እናም እንዲህ አሉት፥ እነሆ እርሱ ፈረሶችህን እያበላ ነው። አሁን ንጉሱ ከብቶቻቸውን ውሃ ከማጠጣታቸው በፊት፣ ፈረሶቹንና ሰረገላዎቹን እንዲያዘጋጁ፣ እናም ወደኔፊ ምድር እንዲወስዱት አገልጋዮቹን አዝዞ ነበር፤ የምድሪቱ ሁሉ ንጉስ በሆነው የላሞኒ አባት በኔፊ ምድር ላይ ታላቅ ግብዣ ተመድቦ ነበርና።

እንዲሁም ንጉስ ላሞኒ አሞን ፈረሶቹንና ሰረገላዎቹን ማዘጋጀቱን በሰማ ጊዜ ይበልጥ በአሞንም ታማኝነት ተደንቆ፣ እንዲህ አለ፥ በእርግጥ እንደዚህ ሰው ከአገልጋዮቼ ሁሉ መካከል ታማኝ አገልጋይ የለም፣ ትዕዛዛቴንም ሁሉ እንኳን ለመፈፀም አስተውሏልና።

፲፩ አሁን በእርግጥ ይህ ታላቁ መንፈስ እንደሆነ አውቃለሁ፤ እናም እርሱ ወደ እኔ እንዲመጣ እፈልጋለሁ፣ ነገር ግን አልደፍርም።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ አሞን ለንጉሱና ለአገልጋዮቹ ፈረሶቹንና ሰረገላዎቹን ካዘጋጀ በኋላ፣ ወደ ንጉሱ ገባ፣ እናም የንጉሱ ፊት እንደተለወጠ ተመለከተ፤ ስለዚህ እርሱም ከፊቱ መመለስ ጀመረ።

፲፫ እናም ከንጉሱ አገልጋዮች አንዱ እንዲህ አለው፥ ራባና፣ ማለትም ሲተረጎም ኃያል ወይንም ታላቅ ንጉስ ነው፤ ንጉሳቸው ኃያል እንደሆነ ይቆጥሩታልና፤ እናም እንዲህ አለው፥ ራባና፣ ንጉሱ እንድትቆይ ይፈልጋል።

፲፬ ስለሆነም አሞን ወደ ንጉሱ በመዞር እንዲህ አለው፥ ንጉስ ሆይ ለአንተ ምን እንዳደርግ ትፈልጋለህ? እናም ንጉስ እንደነርሱ ሰዓት ለአንድ ሰዓት ያህል ምንም አልመለሰለትም፣ ምክንያቱም ለእርሱ ምን ማለት እንዳለበት አላወቀምና።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ አሞን በድጋሚ አለው፥ ከእኔ ምን ትፈልጋለህ? ነገር ግን ንጉሱ ምንም አልመለሰለትም።

፲፮ እናም እንዲህ ሆነ አሞን በእግዚአብሔር መንፈስ በመሞላቱ የንጉሱን ሀሳብ አስተዋለ። እናም እንዲህ አለው፥ ከብቶችህንና አገልጋዮችህን እንደጠበቅኩኝ፣ አገልጋዮችህንና መጋዎችህን ለመከላከል ሰባቱን ወንድሞቻቸውን በወንጭፍና በጎራዴ እንደገደልኩኝ፣ እናም የሌሎችን እጅ የቆረጥኩትን በመስማትህ ነው፤ እነሆ፣ ለአስደናቂ ነገሮችህ መንስኤስ ይህ ነውን?

፲፯ እንዲህ እልሃለሁ፣ ድንቅ ነገሮችህ ታላቅ የሆኑት እንዴት ነው? እነሆ፣ እኔ ሰው ነኝ፣ እናም የአንተ አገልጋይ ነኝ፤ ስለዚህ፣ አንተ የፈለከውን ማንኛውንም ትክክል ነገር አደርጋለሁ።

፲፰ አሁን ንጉሱ እነዚህን ቃላት በሰማ ጊዜ አሞን ሃሳቡን እንደተረዳ ስለተመለከተ በድጋሚ ተደነቀ፤ ነገር ግን ቢሆንም፣ ንጉሱ ላሞኒ አፉን በመክፈት እንዲህ አለው፥ አንተ ማን ነህ? ሁሉንም ነገሮች የሚያውቅ ታላቁ መንፈስ ነህን?

፲፱ አሞን፣ እኔ አይደለሁም በማለት መለሰ።

እናም ንጉሱ እንዲህ አለው፥ ታዲያ የልቤን ሀሳብ እንዴት ልታውቅ ቻልህ? አንተ በድፍረት ተናገርና፣ እነዚህን በተመለከተ ንገረኝ፣ እናም ደግሞ በምን ኃይል ከብቶቼን የበተኑትን ወንድሞቼን እጆች እንደመታሃቸው ንገረኝ—

፳፩ እናም አሁን እነዚህን ነገሮች በተመለከተ የምትናገረኝ ከሆነ፣ የፈለግኸውን ሁሉ አሰጥሃለሁ፤ እናም አስፈላጊ ከሆነ፣ በሠራዊቶቼ እጠብቅሀለሁ፤ ነገር ግን አንተ ከሁሉም በላይ ኃያል እንደሆንክ አውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ፣ ከእኔ የፈለግኸውን ማንኛውንም እሰጥሀለሁ።

፳፪ እንግዲህ አሞን ብልህ ቢሆንም፣ የሚጎዳም ባለመሆኑ፣ ለላሞኒ እንዲህ አለው፥ በምን ሀይል እነዚህ ነገሮች ለማድረግ እንደምችል ብነግርህ ቃሌን ትሰማኛለህን? እናም ይህም ከአንተ የፈለግሁት ነገር ነው።

፳፫ እናም ንጉሱ እንዲህ ሲል መለሰለት፥ አዎን፣ ቃልህን በሙሉ አምናለሁ። እናም እርሱ እንደዚህ ነበር በብልህነት የተያዘው።

፳፬ እናም አሞን በድፍረት ለእርሱ መናገር ጀመረና፣ እንዲህ አለው፥ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህን?

፳፭ እናም እንዲህ ሲል መለሰለት፥ ይህ ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም።

፳፮ እናም አሞን እንዲህ አለው፥ ታላቅ መንፈስ እንዳለ ታምናለህን?

፳፯ እናም እርሱ አዎን አለ።

፳፰ እናም አሞን፣ ይህ እግዚአብሔር ነው አለ። እናም አሞን በድጋሚ አለው፥ ይህ እግዚአብሔር የሆነው ታላቅ መንፈስ በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረ እንደሆነ ታምናለህን?

፳፱ እርሱም አዎን፣ በምድር ላይ ያሉትን ነገሮች ሁሉ እንደፈጠረ አምናለሁ፤ ነገር ግን የሰማያትን አላውቅም።

እናም አሞን እንዲህ አለው፥ ሰማያት እግዚአብሔርና ቅዱሳን መላዕክቱ የሚኖሩበት ቦታ ነው።

፴፩ እናም ንጉስ ላሞኒ እንዲህ አለ፥ ይህ ከመሬት በላይ ነውን?

፴፪ እናም አሞንም አለ፥ አዎን፣ እናም የሰው ልጆችን ሁሉ ወደታች ይመለከታል፤ የልባቸውን ሀሳብና መሻት በሙሉ ያውቃልም፤ ምክንያቱም ከመጀመሪያ ጀምሮ ሁሉም በእጁ ተፈጥረዋልና።

፴፫ እናም ንጉስ ላሞኒ እንዲህ አለ፥ አንተ የተናገርካቸውን እነዚህን ነገሮች ሁሉ አምናለሁ። አንተ ከእግዚአብሔር የተላክህ ነህን?

፴፬ አሞን እንዲህ አለው፥ እኔ ሰው ነኝ፤ እናም በመጀመሪያ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሯል፣ እናም እነዚህን ነገሮች ይህ ህዝብ ትክክልና እውነት ወደ ሆነው እውቀት ይመጡ ዘንድ እንዳስተምር በቅዱስ መንፈሱ ተጠርቻለሁ።

፴፭ እናም እውቀትንና፣ ደግሞ ኃይልን በእግዚአብሔር ላይ ባሉት እምነቴና ፍቃዴ የሚሰጠኝ የመንፈሱ ክፍል ከእኔ ጋር ይኖራል።

፴፮ አሁን አሞን እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፣ ከዓለም መፈጠርና ደግሞ ከአዳም መፈጠር ጀምሮ፣ እናም የሰው መውደቅን በተመለከተ ሁሉም ነገሮች ነገረው፣ እናም አባታቸው ሌሂ ኢየሩሳሌምን ለቆ ከወጣበት ጊዜ ድረስ እንኳ የነበሩትን ታሪኮቹንና በነብያት የተነገሩትን የህዝቡን ቅዱሳት መጻሕፍትን መተረክና መዘርዘር ጀመረ።

፴፯ እናም ደግሞ ለእነርሱ (ይህም ለንጉሱና ለአገልጋዮቹ ነበርና) በምድረበዳ ውስጥ የነበሯቸውን የአባቶቻቸውን ጉዞና የእነርሱን ረሃብና ጥማት እንዲሁም ድካምና ሌሎችንም ሁሉ ስቃያቸውን ነገራቸው።

፴፰ እናም ደግሞ ስለላማንና ልሙኤል፣ ደግሞም ስለእስማኤል ልጆች አመፅ ተናገረ፣ አዎን፣ አመፃቸውን ሁሉ ተረከላቸው፤ እናም ሌሂ ኢየሩሳሌምን ለቆ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን ያሉትን መዛግብቱና ቅዱሳት መጻሕፍት ገለፀላቸው።

፴፱ ነገር ግን ይህ ብቻም አይደለም፣ ከዓለም መፈጠር ጀምሮ ተዘጋጅቶ ስለነበረው የቤዛነትን ዕቅድ አብራራላቸው፤ እናም ስለክርስቶስ መምጣትም አስታወቃቸውና፣ የጌታን ስራዎች ሁሉ እንዲያውቁት አደረገ።

እናም እንዲህ ሆነ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከተናገረ በኋላ፣ እናም ለንጉሱ አብራራቸው፣ ንጉሱም የተናገረውን በሙሉ አመነው።

፵፩ እናም ወደ ጌታ እንዲህ ሲል መጮህ ጀመረ፥ አቤቱ ጌታ ምህረትህን አድርግ፤ በኔፊ ህዝብ ላይ ያደረከውን የበዛ ምህረትን፣ በእኔና በህዝቤ ላይ አድርግ።

፵፪ እናም አሁን፣ ይህንን በተናገረ ጊዜ እንደሞተ ሰው በመሬት ላይ ወደቀ።

፵፫ እናም እንዲህ ሆነ አገልጋዮቹ ወሰዱት፣ ወደ ሚስቱ ተሸክመው ወሰዱትና፣ በአልጋው ላይ አስተኙት፤ እናም ለሁለት ቀንና ምሽት እንደሞተ ሰው ተኛ፤ ሚስቱ፣ ወንድና ሴት ልጆቹም በሃዘን ተቀመጡ፣ እንደ ላማናውያንም በሆነ ወግ ስለእርሱ እጅግ አለቀሱ።