ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፲፯


ለእግዚአብሔር ቃል በመንግስቱ የነበራቸውን መብት የናቁት፣ እናም ላማናውያንን ለመስበክ ወደኔፊ ምድር የሄዱት የሞዛያ ልጆች፣ የስቃያቸውና የመዳናቸው ታሪክ—አልማ እንደመዘገበው።

ምዕራፍ ፲፯ እስከ ፳፯ አጠቃሎ የያዘ።

ምዕራፍ ፲፯

የሞዛያ ልጆች የትንቢትና የራዕይ መንፈስ አላቸው—ቃሉን ለላማናውያን ለማወጅ ወደ ተለያዩ መንገዶች ተጓዙ—አሞን ወደ እስማኤል ምድር ተጓዘ፣ እናም የንጉስ ላሞኒ አገልጋይ ሆነ—አሞን የንጉሱን መንጋዎች አዳነ፣ እናም ጠላቶቹን በሴቡስ ወንዝ ገደለ። ከቁጥር ፩–፫፣ በ፸፯ ም.ዓ. ገደማ፣ ቁጥር ፬፣ ከ፺፩–፸፯ ም.ዓ. ገደማ፤ እናም ከቁጥር ፭–፴፱፣ በ፺፩ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን እንዲህ ሆነ አልማ ከጌዴዎን ምድር ከደቡብ በኩል ወደ ማንቲ ምድር ሲጓዝ፣ እነሆ በመገረም ከሞዛያ ልጆች ጋር ወደ ዛራሔምላ ሲጓዙ ተገናኘ

እንዲሁም የሞዛያ ልጆች መልአኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገለጥለት ከአልማ ጋር ነበሩ፤ ስለዚህ አልማ ወንድሞቹን በመመልከቱ እጅግ ተደሰተ፤ እናም ደስታውን ይበልጥ የጨመረው አሁንም በጌታ ወንድሞቹ በመሆናቸው ነበር፤ አዎን፣ እናም እውነትን በማወቅ የጠነከሩ ነበሩ፤ ትክክለኛ ማስተዋል የነበራቸው፣ የእግዚአብሔርን ቃል ያውቁ ዘንድ ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት የሚያጠኑ ሰዎች ነበሩ።

ነገር ግን ይህ ብቻም አይደለም፤ እራሳቸውን በብዙ ጸሎትና ፆም አተጉ፤ ስለዚህ የትንቢት መንፈስና፣ የራዕይ መንፈስ ነበራቸው፣ እናም በሚያስተምሩበት ጊዜም በእግዚአብሔር ኃይልና ስልጣን አስተማሩ።

እናም የእግዚአብሔርን ቃል በላማናውያን መካከል ለአስራ አራት ዓመታት አስተማሩ፤ እናም ብዙዎችን ወደ እውነት በማምጣት አጥጋቢ ውጤት አግኝተው ነበር፤ አዎን በቃላቸው ኃይልም ስሙን ለመጥራትና በፊቱም ኃጢአታቸውን ለመናዘዝ ብዙዎች በእግዚአብሔር መሰዊያ ፊት ቀረቡ።

አሁን የጉዞአቸው ሁኔታ ይህን ይመስል ነበር፣ በብዛት ተሰቃይተው ነበርና፤ በአካልም ሆነ በአዕምሮ በረሃብ፣ በጥማትና በድካም ብዙ ተሰቃዩ፣ እናም ደግሞ በመንፈስ ብዙ ሰሩ

አሁን ጉዞአቸውም እነዚህ ነበሩ፥ በመሣፍንቱ በመጀመሪያው ዓመት፣ አባታቸው ለእነርሱ ለመስጠት የፈለገውን መንግስት፣ እናም ደግሞ ይህ የህዝቡ ምኞት ነበር፣ ከተቃወሙ በኋላ አባታቸው ሞዛያን ተሰናበቱ

ይሁን እንጂ ከዛራሔምላ ምድር ወጥተው ሄዱ፣ እናም ጎራዴአቸውንና ጦራቸውን፣ ቀስቶቻቸውንና፣ ሻምላቸውን፣ እንዲሁም ወንጭፎቻቸውን ወሰዱ፤ እናም በምድረበዳ ባሉበት ጊዜ ምግባቸውን ያዘጋጁ ዘንድ ይህን አደረጉ።

እናም ወደ ኔፊ ምድር የእግዚአብሔርን ቃል ለላማናውያን ለመስበክ ለመሄድ ከመረጧቸው ጋር ወደ ምድረበዳው ሄዱ።

እናም እንዲህ ሆነ በምድረበዳው ውስጥ ለብዙ ቀናት ተጓዙ፣ እናም ጌታ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ዘንድ መንፈሱን ይሰጣቸው ዘንድና፣ ከእነርሱ ጋር ይቆዩ ዘንድ፣ ወንድሞቻቸው ላማናውያኖችን ወደ እውነት ለማምጣት፣ የሚቻል ከሆነም ትክክል ያልሆነውን፣ የአባቶቻቸውን ወግ መጥፎነቱን ይረዱት ዘንድ በእግዚአብሔር እጅ መሳሪያ እንዲሆኑ በርትተው ፆሙ እንዲሁም ፀለዩ

እናም እንዲህ ሆነ ጌታ በመንፈሱ ጎበኛቸውና፣ እንዲህ አላቸው፥ ተፅናኑ። እነርሱም ተፅናኑ።

፲፩ እናም ደግሞ ጌታ እንዲህ አላቸው፥ ወደ ወንድሞቻችሁ ወደ ላማናውያን ሂዱ፣ ቃሌንም መስርቱ፤ ይሁን እንጂ በእኔ ለእነርሱ መልካም ምሳሌ ታሳዩ ዘንድ በስቃያችሁ ፅናትና ትእግስት ይኑራችሁ፣ እናም ለብዙ ነፍስ መዳኛ በእጆቼ መሳሪያ አደርጋችኋለሁ።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ የሞዛያ ልጆችና፣ ደግሞ ከእነርሱ ጋር የነበሩት፣ ልብ የጌታን ቃል ወደ ላማናውያን በመሄድ ለመናገር ድፍረትን አገኙ።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ በላማናውያን ምድር ዳርቻ በደረሱ ጊዜ፣ በመኽራቸው ወቅትም በኋላ በድጋሚ እንደሚገናኙ በጌታ በማመን እርስ በርስ ተለያዩና፣ አንዱ ከሌላኛው ተከፈሉና ተለዩ፤ ለመስራት በእራሳቸው ላይ የወሰዱት ስራ ታላቅ እንደሆነ ገምተዋልና።

፲፬ እና በእርግጥም ታላቅ ነበር፣ ምክንያቱም የጌታን ቃል ዱር፣ ልበ ጠጣሮችና፣ አስፈሪ ለሆኑ ሰዎች ለመስበክ በእራሳቸው ላይ ወስደውታልና፤ ህዝቡም ኔፋውያንን በመግደልና በመስረቅ እንዲሁም በመዝረፍ የሚደሰት ነበር፤ እናም ልባቸው በሀብት ላይ፣ እንዲሁም በወርቅና በብር፣ እናም በከበሩት ድንጋዮች ላይ የተደገፈ ነበር፤ ይሁን እንጂ እነዚህን ነገሮች በእጃቸው ሳይሰሩ በግድያና በዝርፊያ ማግኘትን ተመኙ።

፲፭ እነርሱ እንደዚህ ከንቱ ሰዎች ነበሩ፣ ብዙዎቻቸው ጣዖትን አምላኪዎች ነበሩ፣ እናም በአባቶቻቸው ባህል የተነሳ የአምላክ እርግማን በእነርሱ አርፎ ነበር፤ ይህም ቢሆን ንስሃ እስከገቡ ድረስ የጌታ ቃል ኪዳን ለእነርሱ ተዘርግተውላቸዋል።

፲፮ ስለዚህ፣ እነርሱም ወደ ንሰሃ፣ እናም ምናልባትም የቤዛነትን ዕቅድ ወደማወቅ ያመጡአቸው ዘንድ፣ ለዚህም ምክንያት ነበር የሞዛያ ልጆች ስራውን በእራሳቸው ላይ የወሰዱት።

፲፯ ስለዚህ እራሳቸውን ከሌላኛው ለዩ፣ እናም ከመካከላቸው ለእነርሱ በተሰጠው በእግዚአብሔር ቃልና ኃይል መሰረት እያንዳንዱ ሰው ብቻውን ሄደ።

፲፰ እንዲሁም አሞን ከመካከላቸው ዋና ስለነበር፣ ወይም እነርሱን ረዳቸው፣ እናም እንደጥሪአቸው መሰረት ከባረካቸውና የጌታን ቃል ካካፈላቸው፣ እናም ከመሄዱም በፊት ከረዳቸው በኋላ ከእነርሱ ተለየ፤ እንደዚህም የተለያዩ ጉዞአቸውን በምድሪቱ አደረጉ።

፲፱ እናም አሞን ወደ እስማኤል ምድር ሄደ፣ ምድሪቱም የተጠራችው ላማናውያን በሆኑት በእስማኤል ልጆች ስም ነበር።

እናም አሞን በእስማኤል ምድር በገባ ጊዜ፣ በእጃቸው የወደቁትን ኔፋውያን ሁሉ ማሰር፣ እናም በንጉሱ ፊት መውሰዳቸው ባህል ስለነበር፣ ላማናውያን ወሰዱትና አሰሩት፤ እናም እንደ ፈቃዱና ደስታው ለመግደል፣ ወይም በምርኮ ለማቆየት፣ ወይም ወደ ወህኒ ለመጣል፣ ወይም ከራሱ አገር ለማስወጣት፣ ንጉሱ እንደ ፍላጎቱ ያደርግ ዘንድ እንደዚህ ይተውለት ነበር።

፳፩ እናም አሞን በእስማኤል ምድር በነገሰው ንጉስ ፊት ተይዞ ቀረበ፤ ስሙም ላሞኒ ይባል ነበር፣ እርሱም የእስማኤል ዝርያ ነበር።

፳፪ እናም በምድሪቱ ከላማናውያን፣ ወይም ከእርሱ ህዝቦች፣ ጋር ለመኖር ፈቃዱ እንደሆነ አሞንን ንጉሱ ጠየቀው።

፳፫ እናም አሞን እንዲህ አለው፥ አዎን፣ ከዚህ ህዝብ ጋር ለተወሰነ ጊዜ፣ አዎን፣ እናም ምናልባት እስከምሞትባት ቀን ድረስ ለመኖር እፈልጋለሁ።

፳፬ እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ላሞኒ በአሞን እጅግ ተደሰተና፣ የታሰረበት እንዲፈታ አደረገ፤ እናም አሞን ከሴት ልጆቹ አንዷን እንዲያገባለት ፈለገ።

፳፭ ነገር ግን አሞን እንዲህ አለው፥ አይሆንም፣ ነገር ግን አገልጋይህ እሆናለሁ። ስለዚህ አሞን ለንጉስ ላሞኒ አገልጋይ ሆነ። እናም እንዲህ ሆነ በላማናውያን ባህል መሰረት የላሞኒን መንጋዎችን ለመጠበቅ ከሌሎች አገልጋዮች ጋር ተሰማራ።

፳፮ እናም ለሶስት ቀናት ንጉሱን ካገለገለ በኋላ፣ የሴቡስ ውሃ ተብሎ ወደሚጠራው ውሃ ወዳለበት ስፍራ ከብቶቻቸውን ከላማናውያን አገልጋዮች ጋር ውሃ ለማጠጣት ሄደ፣ እናም ላማናውያን በሙሉ ከብቶቻቸው ውሃ እንዲያገኙ ወደ እዚህ ቦታ መርተዋቸው ነበር—

፳፯ ስለዚህ፣ አሞንና የንጉሱ አገልጋዮች መንጋዎቻቸውን ወደዚህ የውሃ ስፍራ እየነዱ በወሰዱ ጊዜ፣ እነሆ ወደውሃው ከመንጋዎቻቸው ጋር የነበሩት የተወሰኑ ላማናውያን ቆሙ፣ እናም የአሞንንና የንጉሱ አገልጋዮች መንጋዎችን በታተኑአቸው፣ እናም በብዙ አቅጣጫ እስከሚበታተኑም አባረሩአቸው።

፳፰ እንግዲህ የንጉሱ አገልጋዮች እንዲህ በማለት ማጉረምረም ጀመሩ፥ እንግዲህ ንጉሱ እነዚህ ሰዎች በክፋታቸው መንጋዎቻቸውን በመበተናቸው ምክንያት በወንድሞቻችን ላይ እንዳደረገው ይገድለናል። እናም እንዲህ በማለት በሀይል አለቀሱ፥ እነሆ መንጋዎቻችን ተበትነዋል።

፳፱ እንግዲህ መገደላቸውን ፈርተው አለቀሱ። እንግዲህ አሞን ይህንን በተመለከተ ጊዜ ልቡ በደስታ ተሞላ፤ እንዲህም አለ፥ ለንጉሱ እነዚህን ከብቶች በመመለስ፣ የአገልጋይ ጓደኞቼን ልብ አሸንፍ ዘንድ፣ በቃሌም እንዲያምኑ እመራቸው ዘንድ ለእነዚህ ከእኔ ጋር አገልጋዮች ለሆኑት ኃይሌን፣ ወይንም በውስጤ ያለውን ሀይል አሳያቸዋለሁ።

እናም አሁን፣ እነዚህ ወንድሞቼ በማለት የጠራቸውን ስቃይ በተመለከተ ጊዜ፣ ይህ የአሞን ሀሳብ ነበር።

፴፩ እናም እንዲህ ሆነ እንዲህ በማለት በቃሉ አበረታታቸው፥ ወንድሞቼ፣ አትፍሩም መንጋዎቹን ለመፈለግም እንሂድ፣ እናም በአንድ ላይ እንሰበስባቸዋለን፣ ወደ ውሃው ስፍራ እንመልሳቸዋለንም፣ እንደዚህም መንጋዎቹን ለንጉሱ እንጠብቃለን፣ እርሱም አይገድለንም።

፴፪ እናም እንዲህ ሆነ መንጋዎቹን ፍለጋ ሄዱ፣ አሞንንም ተከተሉት፣ እናም በፍጥነት ሮጡና፣ የንጉሱን መንጋዎች መለሱአቸው፤ በአንድ ላይ ወደ ውሃው በድጋሚ ሰበሰቡአቸው።

፴፫ እናም እነዚያ ሰዎች በድጋሚ ከብቶቹን ለመበታተን ተነሱ፤ ነገር ግን አሞን ለወንድሞቹ እንዲህ አላቸው፥ መንጋዎቹ እንዳይሸሹ ክበቡአቸው፤ እናም እኔ እሄዳለሁና፣ ከብቶቻችንን ከሚያባርሩት ጋር እጣላለሁ።

፴፬ ስለዚህ፣ አሞን እንዳዘዘው አደረጉ፤ እርሱም ሄደና በሴቡስ ውሃ አጠገብ የነበሩትን ለመጣላት ተነሳ፤ እናም እነርሱ በቁጥራቸው ብዙ ነበሩ።

፴፭ ስለዚህ ከእነርሱ አንዱ ሰው እርሱን እንደፈለገው ለመግደል ይችላል በማለት በመገመታቸው አሞንን አልፈሩትም ነበር፣ ጌታ ለሞዛያ ልጆቹን ከእጃቸው እንደሚያወጣ ቃል መግባቱን አላወቁምና፣ ስለጌታም ቢሆን ምንም አያውቁም ነበር፤ ስለዚህ በወንድሞቻቸው ጥፋት ተደሰቱ፤ እናም በዚህ ምክንያት የንጉሱን ከብቶች ለማባረር ተነስተዋል።

፴፮ ነገር ግን አሞን ተነሳ እናም በወንጭፉ ድንጋይ በእነርሱ ላይ መወርወር ጀመረ፤ አዎን፣ በታላቅ ሀይል ድንጋይ በመካከላቸው በወንጭፉ ወረወረ፤ እናም የተወሰኑትን በመግደሉ በሀይሉ መደነቅ ጀምሩ፤ ይሁን እንጂ ወንድሞቻቸው ስለተገደሉባቸው ተቆጡና፣ እርሱ እንዲወድቅ ቆርጠው ነበር፣ ስለዚህ በድንጋዮቻቸው ሊመቱት እንዳልቻሉ በመመልከታቸው ሊገድሉት ዱላቸውን ይዘው መጡ።

፴፯ ነገር ግን፣ እነሆ አሞንን ለመምታት ዱላውን ያነሳ ማንኛውንም ሰው አሞን በጎራዴው እጆቻቸውን መትቶ ቆረጠ፤ እስኪገረሙ ድረስ በጎራዴው ጫፍ እጃቸውን በመምታት ምታቸውን ተቋቋመውና፣ ከፊቱ መሸሽ ጀመሩ፤ አዎን፣ እናም በቁጥር ጥቂት አልነበሩም፤ እናም በክንዱ ጥንካሬም እንዲሸሹ አደረገ።

፴፰ አሁን በወንጭፉ ስድስት ሰዎች ወደቁ፣ ነገር ግን ከመሪያቸው በስተቀር ማንንም በጎራዴው አልገደለም፤ እናም በእርሱ ላይ የተነሱትን እጅ ሁሉ መትቶ ቆረጠ፣ እናም እነርሱ ጥቂት አልነበሩም።

፴፱ እንግዲህ አርቆ ካሸሻቸው በኋላ ተመለሰ፣ እናም ከብቶቻቸውን ውሃ አጠጡአቸውና ወደንጉሱ ግጦሽ መለሱአቸው፣ እናም እርሱን ሊገድሉ የፈለጉትን በአሞን ጎራዴ የተቆረጡትን እጆች ይዘው ወደንጉሱ ሄዱና፣ ላደረጉአቸው ነገሮች ምስክር እንዲሆኑ ወደ ንጉሱ ተወሰዱ።