ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፩


መፅሐፈ አልማ
የአልማ ልጅ

የአልማ ልጅ፣ በኔፊ ህዝብ ላይ የመጀመሪያውና ዋናው ዳኛ፣ እናም ደግሞ የቤተክርስቲያኗ ሊቀ ካህን የሆነው፣ የአልማ ታሪክ። የመሣፍንት የንግስ፣ እናም በህዝቡ መካከል የነበረው የጦርነትና ፀብ ታሪክ። እናም ደግሞ የመጀመሪያውና ዋናው ዳኛ በሆነው በአልማ መዝገብ መሰረት በኔፋውያንና በላማናውያን መካከል የነበረው የጦርነት ታሪክ።

ምዕራፍ ፩

ኔሆር ሀሰተኛ ትምህርት አስተማረ፣ ቤተክርስቲያንን አቋቋመ፣ የካህን ተንኮልን ጀመረ፣ እናም ጌዴዎንን ገደለው—ኔሆር የተሰቀለው በወንጀሉ ነው—የካህን ተንኮልና ስደት በህዝቡ መካከል ተስፋፋ—ካህናት ራሳቸውን በራሳቸው ይረዳሉ፣ ህዝቡ ለድሆች እንክብካቤ አደረጉ፣ እናም ቤተክርስቲያኗ በለፀገች። ከ፺፩–፹፰ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ መሳፍንቶች በኔፊ ህዝብ ላይ በነገሱበት በመጀመሪያው ዓመት፣ ንጉስ ሞዛያ በቦታውም ማንም እንዲነግስ ሳያደርግ፣ ምድር ሁሉ ወደሚሄዱበት ሄዷል፣ መልካሙን ገድል ተጋድሏል፣ በእግዚአብሔር ፊት በልበ ቅንነት ተራምዷል፤ ይሁን እንጂ ህግጋትን አቋቁሟል፣ እናም እነርሱም በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተዋል፣ ስለሆነም፣ ከዚህም ጊዜ በኋላ፣ ህዝቡ እርሱ ባቋቋመው ህግጋት ለመገዛት ተገደው ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ በአልማ በዳኝነት መቀመጫ ላይ በሚነግስበት በመጀመሪያው ዓመት፣ አንድ ሰው እንዲፈረድበት ወደ ፍርድ ወንበሩ አምጥተውት ነበር፤ ሰውየውም ትልቅ የነበረ እና በጥንካሬውም የሚታወቅ ነበር።

እናም ይህ ሰው ከህዝቡ መካከል በመሄድ እርሱ የእግዚአብሔር ቃል ብሎ ያለውን በመስበክ፣ የቤተክርስቲያኗ ተቃራኒ በመሆን፣ ለህዝቡም ካህንና መምህር ሁሉ ታዋቂ መሆን እንዳለባቸው፣ እናም በእጃቸውም መስራት እንደሌለባቸው፣ ነገር ግን በህዝቡ መደገፍ እንዳለባቸው ያውጅ ነበር።

እናም ደግሞ ለህዝቡ የሰው ዘር ሁሉ በመጨረሻው ቀን መዳን እንዳለበት፣ እናም መፍራትም ሆነ መንቀጥቀጥ እንደሌለባቸው፣ ነገር ግን ጌታ ሁሉን በመፍጠሩና ደግሞም ሁሉን በማዳኑ እራሳቸውን በማቅናት እንዲደሰቱ፣ እንዲሁም በመጨረሻ ሁሉም ሰው ዘለአለማዊ ህይወት ሊኖረው ይገባል በማለት መሰከረ።

እናም እንዲህ ሆነ እነዚህን ነገሮች በብዛት አስተምሮ ብዙዎች የእርሱን ቃላት አመኑ፣ ይህም ሆኖ ብዙዎች እንኳን እርሱን መደገፍ እናም ገንዘብ ይሰጡት ጀመር።

እናም በልቡ ኩራት መወጠር፣ እናም ውድ ልብስ መልበስ ጀመረ፤ አዎን፣ እናም ከሰበካው ጋር በሚዛመድ ሁኔታ እንኳን ቤተክርስቲያንን ማቋቋም ጀመረ።

እናም እንዲህ ሆነ በቃሉ ላመኑት ለመስበክ በመጓዝ ላይ እንዳለ በእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን አባል፣ አዎን፣ የእነርሱም መምህር የነበረ፣ አንድን ሰው አገኘ፤ እናም የቤተክርስቲያኗን ሰዎችም ይለውጣቸው ዘንድ፣ ከእርሱ ጋር በኃይል መከራከር ጀመረ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቃል በመገሰፅ ሰውየው ተቃወመው።

የሰውየው ስምም ጌዴዎን ነበር፤ እናም የሊምሂን ህዝብ ከባርነት ለማስለቀቅ በእግዚአብሔር እጅ መሳሪያ የነበረው እርሱ ነበር።

አሁን ጌዴዎን በእግዚአብሔር ቃል ስለተቃወመው በጊድዮን ተቆጣ፤ እናም ጎራዴውን መዘዘና ይመታው ጀመረ። እንግዲህ ጌዴዎን በማርጀቱ ምቱን ለመቋቋም አልቻለም ነበር፣ ስለሆነም በጎራዴው ሞተ

እናም ገዳዩ በቤተክርስቲያኗ ሰዎች ተወሰደ፣ እናም በፈፀመው ወንጀል እንዲፈረድበት በአልማ ፊት ቀረበ።

፲፩ እናም እንዲህ ሆነ ከአልማ ፊት ቆመና በታላቅ ድፍረት ለራሱ ተከራከረ።

፲፪ ነገር ግን አልማ እንዲህ ሲል ተናገረው፥ እነሆ በዚህ ህዝብ መካከል የካህን ተንኮል ከተጀመረበት ጊዜ ይህ የመጀመሪያው ነው። እናም እነሆ አንተ በካህን ተንኮል ብቻ አይደለም ጥፋተኛ የሆንከው፣ ነገር ግን ይህን በጎራዴው ለማስገደድ ጥረት አድርገሀል፤ እናም የካህን ተንኮል በህዝቡ መካከል በግዴታ የሚደረግ ቢሆን ይህም አጠቃላይ ጥፋታቸውን ያስከትላል።

፲፫ እናም አንተ የፃድቁን ደም አፍስሰሀል፣ አዎን፣ በዚህ ህዝብ መካከል ብዙ መልካምን ያደረገውን ሰው፤ እናም አንተን እንድትተርፍ ካደረግን የእርሱ ደም ለበቀል በእኛ ላይ ይመጣል።

፲፬ ስለሆነም የመጨረሻው ንጉሳችን በሆነው በሞዛያ በተሰጠን ህግ መሰረት እንድትሞት ተፈርዶብሀል፤ እናም ህጉ በህዝቡ ተቀባይነት አግኝቶኣል፤ ስለዚህ ህዝቡ በህጉ መተዳደር አለበት።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ እርሱንም ወሰዱት፤ ስሙም ኔሆር ነበር፤ እናም ወደ ማንቲ ኮረብታ ጫፍ ወሰዱት፤ እናም በእዚያ ለህዝቡም ያስተማረው ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ተቃራኒ እንደነበረ በሰማይና በምድር መካከል ተቀባይ እንዲሆን ተገደደ ወይም ተቀበለ፤ እናም በእዚያም በአሳፋሪ ሞት ተሰቃየ።

፲፮ ይሁን እንጂ፣ ይህ የካህን ተንኮል በምድሪቱ እንዳይስፋፋ ገደብ አልሆነም፣ ምክንያቱም የዓለምን ከንቱ ነገሮች የሚያፈቅሩ ብዙዎች ነበሩና፣ እናም ሐሰተኛ ትምህርቶችን በመስበክ ሄዱ፤ እናም ይህንን ያደረጉት ለሀብትና ለክብራቸው ነበር።

፲፯ ይሁን እንጂ፣ ህጉን በመፍራት ለመዋሸት አይደፍሩም ነበር፣ ምክንያቱም ይህ ቢታወቅ ኖሮ ሀሰተኞች ይቀጣሉና፤ ስለሆነም በእምነታቸው እንደሚሰብኩ ያስመስላሉ፤ እናም አሁን ህጉ በማንኛውም ሰው እምነት ላይ ስልጣን ሊኖረው አይችልም።

፲፰ እናም ህጉን በመፍራት ለመስረቅ አልደፈሩም፤ እንደነዚህ አይነቶች ተቀጥተዋልና፤ ለመዝረፍም ሆነ፣ ለመግደል አልደፈሩም፣ የገደለ በሞት ይቀጣልና።

፲፱ ነገር ግን እንዲህ ሆነ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን አባል ያልሆኑት የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን አባል የሆኑትን፣ እናም በራሳቸው ላይ የክርስቶስን ስም የለበሱትን አሳደዱ።

አዎን እነርሱንም አባረሩአቸው፣ እናም በሁሉም ዓይነት ቃላት አሰቃዩአቸው፣ ይህም በትህትናቸው የተነሳ፣ እናም በአመለካከታቸው ኩሩ ስላልነበሩና፣ የእግዚአብሔርን ቃል ያለገንዘብና ያለምንም ክፍያ አንዳቸው ለሌላኛው የሚካፈሉ ስለነበሩ ነው።

፳፩ እንግዲህ በቤተክርስቲያኗ አባል የሆነ ማንም ሰው በቤተክርስቲያኗ አባል ያልሆኑትን ተነስቶ የሚያሳድድ መኖር እንደሌለበት፣ እናም በመካከላቸውም ምንም ስደት መኖር እንደሌለበት በቤተክርስቲያኗ ሰዎች መካከል ህጉ ጥብቅ ነበር።

፳፪ ይሁን እንጂ፣ ከእነርሱ መካከል ብዙ መኩራት የጀመሩ፣ እናም ከጠላቶቻቸው ጋር፣ እስከመመታታትም ድረስ፣ በኃይል መጣላት የጀመሩ ነብሩ፣ አዎን፣ በቡጢም አንዱ በሌላኛው ይመታታሉ።

፳፫ አሁን ይህ በአልማ ሁለተኛው የንግስ ዓመት ውስጥ ነበር፤ እናም ለቤተክርስቲያኗ ታላቅ ስቃይ ምክንያት ነበር፤ አዎን፣ ለቤተክርስቲያኗ ታላቅ ፈተና ምክንያት ነበር።

፳፬ የብዙዎች ልብ ጠጥሯል፣ እናም ከእንግዲህ በእግዚአብሔር ሰዎች መካከል እንዳይታወሱም ስማቸው ተደምሠዋልና። እናም ደግሞ ብዙዎች ራሳቸውን ከመካከላቸው አወጡ

፳፭ አሁን በእምነታቸው ፀንተው ለቆሙ ይህ ታላቅ ችግር ነበር፤ ይሁን እንጂ፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በመጠበቅ ፅኑና የማይነቃነቁ ነበሩ፣ እናም በላያቸው ላይ የተቆለለውን ጭቆና በትዕግስት ተወጡ።

፳፮ እናም ካህናት የእግዚአብሔርን ቃል ለህዝቡ ለመናገር ስራቸውን በተዉ ጊዜ፣ ሰዎቹም ቢሆኑ የእግዚአብሔርን ቃል ለማዳመጥ ስራቸውን ትተዋል። እናም ካህናት የእግዚአብሔርን ቃል በተናገሩ ጊዜ በድጋሚ ወደ ስራዎቻቸው በትጋት ተመለሱ፤ እናም ካህኑም፣ እራሱን ከአድማጩ በላይ አላደረገም፣ ምክንያቱም ሰባኪው ከአድማጩ የተሻለ፣ መምህሩም ከተማሪው ምንም የተሻለ አልነበረም፤ እናም ሁሉም እኩል ነበሩና፣ ሁሉም ሰዎች በጥንካሬአቸው መሰረት ስራቸውን ይሰራሉ።

፳፯ እናም ማንኛውም ሰው ለድሆችና ለችግረኞች፣ እናም ለታመሙና፣ ለተሰቃዩት ባላቸው መጠን ከቁሳቁሶቻቸው አካፈሉ፤ እናም እነርሱ ውድ ልብሶችን አልለበሱም ነበር፣ ይሁን እንጂ ንፁህና የደስደስ ያላቸው ነበሩ።

፳፰ እና እንደዚህም የቤተክርስቲያን ጉዳዮችን አቋቋሙ፤ እና እንደዚህም ይህ ሁሉ ጭቆና ቢኖርባቸውም የማያቋርጥ ሰላም በድጋሚ ይኖራቸው ጀመር።

፳፱ እናም አሁን፣ በቤተክርስቲያኗ ፅኑነት የተነሳ እጅግ ሀብታም መሆን ጀመሩ፣ ሁሉም የሚያስፈልጋቸው ማንኛውም ነገሮች በብዛት ነበራቸው—ብዙ መንጋዎችና ከብቶች፣ ሁሉም ዓይነት ኮርማዎችም፣ ደግሞም ብዙ ጥራጥሬና፣ ወርቅ፣ ብርና፣ የከበሩ ነገሮች፣ እናም ብዙ ሐርና የተፈተለ ጥሩ በፍታ፣ እናም ሁሉም ዓይነት መልካም ልብሶች ነበሯቸው።

እናም እንዲሁ፣ በብልፅግናቸው የተራቁትን ወይም የተራቡትን፣ ወይም የተጠሙት፣ የታመሙትን ወይም ያልተመገቡትን ቢሆን ማንንም አላባረሩም፤ እናም ልባቸውን በሀብት ላይ አላደረጉም፤ ስለዚህ ለሁሉም፣ ለወጣቶችም ሆነ ለሽማግሌዎች፣ ለታሰሩትም ሆነ ነፃ ለሆኑት፣ ለወንድም ሆነ ለሴት፣ ከቤተክርስቲያን ለሆኑም ሆነ ላልሆኑት ደግ ነበሩ፤ በችግር ለነበሩት እንዳደረጉት ሁሉ በሰዎች ፊት አላደሉም

፴፩ እናም በለፀጉና ከእነርሱ ቤተክርስቲያን ካልሆኑት በበለጠ ሀብታም ሆኑ።

፴፪ ከእነርሱ ቤተክርስቲያን ያልሆኑት ራሳቸውን በጥንቆላና በጣኦት አምላኪነት ወይም በስንፍና እናም በከንቱ ልፍለፋ እናም በቅናትና ክርክር፣ ውድ ልብሶችን በመልበስ፣ በትዕቢት በራሳቸው አይን በመነፋት፣ በማሳደድ፣ በመዋሸት፣ በመስረቅ፣ በመዝረፍ፣ ዝሙትን በመፈፀምና፣ በመግደል፣ እናም ሁሉንም ዓይነት ኃጢያት በመፈፀም ራሳቸውን አስደሰቱ፤ ይሁን እንጂ፣ ህጉ በሚቻለው መጠን በተላለፉት ሁሉ ላይ በኃይል ተደርጓል።

፴፫ እናም እንዲህ ሆነ እንደዚህ ህግን በእነርሱ ላይ በማሳረፍ፣ እያንዳንዱ ሰው በሰራው መሰረት እየተቀጣ፣ እነርሱም ይበልጥ ተረጋጉ፣ እናም የሚታወቅ ከሆነ ምንም ዓይነት ኃጢያት ለመፈፀም አልደፈሩም፤ ስለዚህ፣ እስከ አምስተኛው ዓመት የመሳፍንት አገዛዝ ድረስ በኔፊ ህዝቦች መካከል ከፍተኛ ሰላም ነበር።