ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፳፮


ምዕራፍ ፳፮

ኢየሱስ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻው ያሉትን ነገሮች በሙሉ አብራራ—ህፃናት እንዲሁም ልጆች ሊፃፉ የማይችሉ አስደናቂ ነገሮችን ተናገሩ—በክርስቶስ ቤተክርስቲያን የነበሩት በመካከላቸው ሁሉም ነገሮች በጋራ ነበሩአቸው። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች በተናገራቸው ጊዜ እነዚህን ለህዝቡ አብራራ፤ እናም ትልቅ እንዲሁም ትንሽ የሆኑትን ሁሉንም ነገሮች አብራራላቸው።

እናም እንዲህ አለ፥ እናንተ የሌላችሁን እነዚህ ቅዱሳን መጽሐፍት አብ እንድሰጣችሁ አዟል፤ ለመጪው ትውልድ መስጠት እንደሚገባቸው የእርሱ ጥበብ ነው።

እናም ከመጀመሪያው ጀምሮ በክብሩ እስከሚመጣ ድረስ ያሉትን ሁሉንም ነገሮች—አዎን፣ በምድር ገፅ ላይ የሚመጡትን ነገሮች ሁሉ፣ የምድር ማዕድናትም በታላቅ ሙቀት እስከሚቀልጡ ድረስና፣ ምድርም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል እስከምትጠቀለል፣ እናም ሰማይና ምድርም እስከሚያልፉ እንኳን አብራራላቸው፤

እናም ሀገር ሁሉ፣ እናም ነገዶች ሁሉ፣ እናም ሁሉም ህዝቦችና ቋንቋ በሙሉ መልካም ይሁኑም መጥፎ፣ እንደስራቸው እንዲፈረድባቸው በእግዚአብሔር ፊት ስለሚቆሙበት ታላቁና በመጨረሻው ቀንም እንኳን—

መልካም ከሆኑም፣ ለዘለዓለማዊው ህይወት ትንሳኤ፤ ክፉ ከሆኑም፣ ወደኩነኔም ትንሳኤ፤ ከአለም በፊት በነበረው ክርስቶስ ምህረትና፣ ፍትህ፣ እና ቅድስና መሰረት፣ አንደኛው በአንድ እጅ እናም ሌላኛው በሌላ እጅ በመሆን እነዚህ የተገናኙ ናቸው።

እናም እንግዲህ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ኢየሱስ በእውነት ለህዝቡ ካስተማራቸው ነገሮች አንድ መቶኛው እንኳን ሊፃፍ አልተቻለም፤

ነገር ግን እነሆ የኔፊ ሠሌዳዎች ህዝቡን ስላስተማራቸው ነገሮች በይበልጥ ይዘዋል።

እናም እኔ የጻፍኳቸው እነዚህ ነገሮች፣ እርሱ ካስተማራቸው ነገሮች ጥቂቶች ናቸው፤ እናም እነርሱም ኢየሱስ በተናገራቸው ቃላት መሰረት እነዚህ ለዚህ ህዝብ በድጋሚ ከአህዛብ ይመጡ ዘንድ ፅፌአቸዋለሁ።

እናም እምነታቸውን በመጀመሪያ እንዲፈትኑበት ይህን መቀበላቸው አስፈላጊ ስለሆነ፣ ይህን በተቀበሉበት ጊዜ፣ እናም እነዚህን ነገሮች የሚያምኗቸው ከሆነ ከዚያም ታላላቅ የሆኑት ነገሮች ይገለፁላቸዋል።

እናም እነዚህን ነገሮች የማያምኑ ከሆኑ፣ ታላላቆቹ ነገሮችም እነርሱን ይኮንኑ ዘንድ አይገለፁላቸውም

፲፩ እነሆ፣ በኔፊ ሠሌዳዎች ላይ የተፃፉትን ሁሉ ለመፃፍ ተዘጋጅቼ ነበር፣ ነገር ግን ጌታ እንዲህ በማለት ከልክሎኛል፥ የህዝቤን እምነት እፈትናለሁ

፲፪ ስለዚህ እኔ ሞርሞን፣ በጌታ የታዘዝኩባቸውን ነገሮች እፅፋለሁ። እናም እንግዲህ እኔ ሞርሞን ንግግሬን አበቃለሁ፤ እናም የታዘዝኳቸውን ነገሮች መፃፌን እቀጥላለሁ።

፲፫ ስለዚህ፣ ጌታም ለሶስት ቀናት በእውነት ህዝቡን እንዳስተማረ እንድትመለከቱ እፈልጋለሁ፤ እናም ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ ራሱን አሳይቷቸዋል፣ እናም በተደጋጋሚም ዳቦ በመቁረስ ባርኮ ሰጥቷቸዋል።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ የተነገረላቸውን ሰዎች ልጆችም ኢየሱስ አስተማራቸውና አገለገላቸው፣ እናም አንደበታቸውን ፈታላቸውና፣ ለህዝቡ እርሱ ከገለፀላቸው የበለጡትን ለአባቶቻቸው ታላቅና አስገራሚ የሆኑ ነገሮችን ተናገሩ፤ እናም ለመናገር እንዲችሉም አንደበታቸውን ፈታላቸው

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ወደ ሰማይም ካረገ በኋላ—ለሁለተኛ ጊዜ እራሱን ገለፀላቸው፣ እናም በሽተኞቻቸውንና ሽባዎችን በሙሉ ከፈወሰና፣ የዕውሮችን ዐይን ካበራ፣ እናም የደንቆሮን ጆሮዎች ከከፈተና፣ ሁሉንም ዐይነት ፈውሶች በመካከላቸው ካደረገ በኋላ፣ እናም አንድን ሰው ከሞት ካስነሳና ኃይሉንም ካሳያቸው በኋላ ወደአብ ሄደ—

፲፮ እነሆ፣ እንዲህ ሆነ በሚቀጥለው ቀን ህዝቡ በአንድ ላይ ተሰበሰበ፣ እናም እነዚህን ልጆች ተመለከቱአቸውና፣ አዳመጡአቸው፤ አዎን፣ ህፃናቱም አፋቸውን ከፈቱና፣ አስደናቂ ነገሮችን ተናገሩ፤ እናም የተናገሩአቸውን ነገሮች ማንም እንዳይፅፍ ተከልክሏል።

፲፯ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ የመረጣቸው ደቀመዛሙርት ከዚያን ጊዜ በኋላ ወደ እነርሱ የመጡትን ሰዎች ሁሉ ማጥመቅና ማስተማር ጀመሩ፤ እናም በኢየሱስ ስም የተጠመቁት ሰዎች በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ነበር።

፲፰ እናም ብዙዎች ሊፃፉ በህግ ያልተፈቀዱትን፣ ሊነገሩ የማይችሉ ነገሮችን ተመልክተዋልም፣ ሰምተዋልም።

፲፱ እናም አንዳቸው ሌላኛውን አገለገሉና፣ አስተማሩ፤ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰውም እርስ በርሱ በፍትህ በማገልገል፣ በመካከላቸው ሁሉም ነገሮች በጋራ ነበሩአቸው።

እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እንዳዘዛቸው ሁሉንም ነገሮች አደረጉ።

፳፩ እናም በኢየሱስ ስም የተጠመቁት የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ተብለው ይጠሩ ነበር።