ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፲፰


ምዕራፍ ፲፰

ኢየሱስ በኔፋውያን መካከል ቅዱስ ቁርባንን ጀመረ—ሁል ጊዜም በስሙ እንዲጸልዩ ታዘዙ—ብቁ ሳይሆኑ ስጋውን የሚበሉ እናም ደሙን የሚጠጡ ይኮነናሉ—ደቀመዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጡ ስልጣን ተሰጣቸው። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ ጥቂት ዳቦ እና ወይን ወደ እርሱ እንዲያመጡ አዘዛቸው።

እና እነርሱ ዳቦውንና ወይኑን ለማምጣት በሄዱበት ጊዜ፣ ህዝቡን በመሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ።

እናም ደቀመዛሙርቱ ዳቦውንና ወይኑን ይዘው በመጡ ጊዜ፣ ከዳቦው ወስዶ በመቁረስ ባረከው፤ እናም ለደቀመዛሙርቱም ሰጣቸውና እንዲበሉትም አዘዛቸው።

እናም በበሉና በተሞሉ ጊዜ፣ ለህዝቡ እንዲሰጡ አዘዘ።

እናም ህዝቡም በልተው በተሞሉ ጊዜ፣ ለደቀመዛሙርቱ እንዲህ አላቸው፥ እነሆ ከመካከላችሁ አንዱ ይሾማል፤ እናም በስሜ ለሚያምኑትና ለሚጠመቁት ለቤተክርስቲያኔ ህዝቦች ዳቦውን እንዲቆርሰውና በመባረክ እንዲሰጣቸው ስልጣንን እሰጠዋለሁ።

እናም እኔ እንዳደረግሁትም ቢሆን፣ እንዲሁም እኔም ዳቦውን እንደቆረስኩትና እንደባረክሁት እናም ለእናንተ እንደሰጠኋችሁ ይህንን ሁል ጊዜ በቀጣይነት አድርጉ።

እናም ይህንን ያሳየኋችሁን ስጋዬን ለማስታወስ አድርጉ። ይህም ሁልጊዜ እኔን እንደምታስታውሱ ለአብ ለምስክርነት ይሆናል። እናም ሁልጊዜ የምታስታውሱኝ ከሆነ መንፈሴ ከእናንተ ጋር ይሆናል።

እናም እንዲህ ሆነ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፣ ደቀመዛሙርቱን ከወይኑ በጥቂቱ እንዲወስዱና ከፅዋውም እንዲጠጡ፣ እናም ደግሞ ህዝቡም ይጠጡ ዘንድ እንዲሰጡአቸው አዘዛቸው።

እናም እንዲህ ሆነ የተባሉትን አደረጉ፣ ከዚህም ጠጡና ተሞሉ፤ ለህዝቡም ሰጡ፣ እናም እነርሱም ጠጡና ተሞሉ።

እናም ደቀመዛሙርቱም ይህንን ባደረጉ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ ስላደረጋችሁት ስለእነዚህ ነገሮች ተባርካችኋል፤ ምክንያቱም ይህ ትዕዛዛቴን መፈፀም ነው፣ እናም ይህም ያዘዝኳችሁን ለመፈፀም ፈቃደኞች መሆናችሁን ለአብ ይመሰክራል።

፲፩ እናም ይህን ንሰሃ ለገቡትና በስሜ ለተጠመቁት ሁልጊዜ ታደርጉታላችሁ፣ እናም ይህንንም ለናንተ ያፈሰስኩትን ደም ለማስታወስ፤ እኔን ሁልጊዜ እንደምታስታውሱኝ ለአብ ለመመስከር ታደርጉታላችሁ። እናም ሁልጊዜም የምታስታውሱኝ ከሆነ መንፈሴ ከእናንተ ጋር ይሆናል።

፲፪ እናም እነዚህን ነገሮች እንድታደርጉ ትዕዛዛትን እሰጣችኋለሁ። እናም እነዚህን ነገሮች ሁል ጊዜ የምታደርጉ ከሆነ፣ የተባረካችሁ ናችሁ፣ በአለት ላይ ቤታችሁን ሰርታችኋልና።

፲፫ ነገር ግን ከእናንተ መካከል ከዚህ የበለጠም ሆነ ያነሰ የሚሰራ፣ በአለቴ ላይ ቤቱን አልሰራም፣ ነገር ግን በአሸዋ ላይ መሰረቱን ሰርቷል፤ እናም ዝናብ በሚወርድበትና የጥፋት ውሀ በሚመጣበት፣ እናም ነፋስ በሚነፍስበትና፣ በሚመታቸው ጊዜ ይወድቃሉ፣ እናም የገሃነም ደጆችም እነርሱን ለመቀበል ክፍት ይሆናሉ።

፲፬ ስለዚህ ለእናንተ እንድሰጣችሁ አብ ያዘዘኝን ትዕዛዛት የምትጠብቁ ከሆነ እናንተ የተባረካችሁ ናችሁ።

፲፭ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ዘወትር ንቁ መሆን እና መፀለይ አለባችሁ፤ አለበለዚያ በዲያብሎስ ትፈተናላችሁ እናም የእርሱ ምርኮኛም ትሆናላችሁ።

፲፮ እናም በመካከላችሁ እንደጸለይኩት እናንተም ንሰሃ በገቡትና በስሜ በተጠመቁት ህዝቦቼ መካከል በቤተክርስቲያኔ በተመሳሳይ ፀልዩ። እነሆ እኔ ብርሃን ነኝ፤ ምሳሌም ትቼላችኋለሁ።

፲፯ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፣ ወደ ህዝቡ በመዞር እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥

፲፰ እነሆ፣ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ እንዳትፈተኑ ዘወትር መንቃት እናም መፀለይ አለባችሁ፤ ምክንያቱም ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ይፈልጋችኋልና።

፲፱ ስለዚህ ዘወትር በስሜ ወደ አብ መፀለይ ይኖርባችኋል፤

እናም በስሜ ትክክል የሆነውን ማንኛውንም ነገር በእምነት እናገኛለን በማለት አብን ከጠየቃችሁት፤ እነሆ ለእናንተ ይሰጣችኋልና።

፳፩ ሚስቶቻችሁ እና ልጆቻችሁ ይባረኩ ዘንድ፣ ዘወትር ከቤተሰቦቻችሁ ጋር በስሜ ፀልዩ

፳፪ እናም እነሆ፣ ዘወትር በአንድነት ተሰባሰቡ፣ እናም በአንድነት በምትሆኑበት ጊዜ ማንም ሰው ወደእናንተ እንዳይመጣ አትከልክሉ፤ ነገር ግን ወደ እናንተ ይመጡ ዘንድ ፍቀዱላቸውና አትከልክሉአቸው፤

፳፫ ነገር ግን ለእነርሱ ፀልዩላቸውና፣ አታባርሩአቸው፤ እናም ዘወትር ወደ እናንተ የሚመጡ ከሆነ ወደ አብም በስሜ ፀልዩላቸው።

፳፬ ስለዚህ፣ ለዓለም ያበራ ዘንድ ብርሃናችሁን ከፍ አድርጉ። እነሆ፣ እኔ ሳደርግ የተመለከታችሁትም፣ እናንተ ከፍ የምታደርጉት ብርሃን ነኝ። እነሆ ወደ አብ መፀለዬን ተመልክታችኋል፣ እናም ሁላችሁም መስክራችኋል።

፳፭ እናም ማናችሁም ከዚህ እንዳትርቁ ማዘዜን ተገንዝባችኋል፤ ነገር ግን ትዳስሱና ትመለከቱ ዘንድ ወደ እኔ እንድትመጡ አዝዣችኋለሁ፤ በዚሁም ሁኔታ ለዓለም አድርጉ፤ እናም ይህንን ትዕዛዝ የሚያፈርስ ቢኖር ወደ ፈተናው ለመግባት ለራሱ ፈቅዷል።

፳፮ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፣ በድጋሚ ወደመረጣቸው ደቀ መዛሙርት ዐይኑን አደረገ፣ እናም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥

፳፯ እነሆ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ሌላ ትዕዛዝ እሰጣችኋለሁ፣ እናም አብም የሰጠኝን ሌሎች ትዕዛዛትን እፈፅም ዘንድ ወደ አባቴ መሄድ ይገባኛልና።

፳፰ እናም እንዲህ ሆነ እነሆ፣ ለእናንተ የምሰጣችሁ ትዕዛዝ ይህ ነው፤ ቅዱስ ቁርባን በምታቀርቡበት ጊዜ ለማንም ስጋና ደሜን ያለብቁነት እንዲወስድ አትፍቀዱ፤

፳፱ ያለብቁነት ስጋዬን የሚበላ እናም ደሜን የሚጠጣ ለነፍሱ እርግማንን ይበላልና ይጠጣል፤ ስለዚህ አንድ ሰውም ስጋዬን እንደሚበላና ደሜን እንደሚጠጣ ብቁ እንዳልሆነ ካወቃችሁ ከልክሉት።

ይሁን እንጂ፣ ከመካከላችሁ አታስወጡት፣ ነገር ግን እርሱን አገልግሉትና በስሜ ወደ አብ ፀልዩለት፤ እናም በስሜ ንሰሃ ከገባና ከተጠመቀ ተቀበሉት እናም ስጋዬንና ደሜን አቅርቡለት።

፴፩ ነገር ግን ንሰሃ ካልገባ፣ ህዝቦቼን እንዳያጠፋ፣ ከህዝቦቼ መካከል አይቆጠርም፣ እነሆ በጎቼን አውቃቸዋለሁ፣ እናም እነርሱም ተቆጥረዋል።

፴፪ ይሁን እንጂ፣ ከምኩራባችሁም ሆነ ከማምለኪያ ስፍራዎቻችሁ አታስወጡ፣ ምክንያቱም ለእነዚህ አይነት ለማገልገል መቀጠል አለባችሁ፤ ምክንያቱም አንድ ቀን እንደሚለወጡና ንሰሃ እንደሚገቡ እናም በልባቸው ሙሉ አላማ ወደ እኔ እንደሚመጡ አታውቁምና፣ እናም እፈውሳቸዋለሁ፤ እናንተም ደህንነትን ወደ እነርሱ ለማምጣት መሳሪያ ትሆናላችሁ።

፴፫ ስለዚህ ወደ ፍርድ እንዳትመጡ እነዚህን ያዘዝኳችሁን ቃላት ጠብቁአቸው፤ አብ ለሚፈርድበት ለዚያ ሰው ወዮለት።

፴፬ እናም በመካከላችሁ በነበረው ፀብ ምክንያት እነዚህን ትዕዛዛት እሰጣችኋለሁ። እናም በመካከላችሁ ፀብ ከሌለ እናንተ የተባረካችሁ ናችሁ።

፴፭ እናም አሁን ለእናንተ ስልም ወደ አብ መሄዴ አስፈላጊ በመሆኑ ወደ አብ እሄዳለሁ።

፴፮ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ ይህንን ንግግሩን በጨረሰ ጊዜ፣ የመረጣቸውን ደቀመዛሙርት ሁሉንም እስከሚነካ ድረስ አንድ በአንድ በእጁ ነካቸውና፣ እንደነካቸውም ተናገራቸው።

፴፯ እናም ህዝቡም የተናገረውን ቃላት አልሰሙትም፤ ስለዚህ አልመሰከሩም፤ ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጡ ስልጣንን እንደሰጣቸው መሰከሩ። እናም ከዚህ ጊዜ በኋላም ይህ ምስክርነት እውነት መሆኑንም አሳያችኋለሁ።

፴፰ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ ሁሉንም በነካቸው ጊዜ፣ ደመና መጣና ህዝቡን ሸፈነው ስለዚህ ኢየሱስን ለማየት አልቻሉም።

፴፱ እናም በተሸፈኑ ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ሔደና፣ ወደ ሰማይ አረገ። እናም ደቀመዛሙርቱ ተመለከቱትና በድጋሚ ወደ ሰማይ ማረጉንም መሰከሩ።