ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፲፬


ምዕራፍ ፲፬

አትፍረዱ፤ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ ከሃሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ በማለት ኢየሱስ አዘዘ—የአባታቸውን ፈቃድ ለሚያደርጉ የደህንነትን ቃል ገብቶላቸዋል—ማቴዎስ ፯ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

እናም አሁን እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ በድጋሚ ወደ ህዝቡ ተመለሰ፣ እናም በድጋሚ አፉን ከፍቶ እንዲህ አላቸው፥ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ

በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፤ እናም በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ደግሞም ይሰፈርላችኋል።

እናም በወንድማችሁ ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያላችሁ፤ ነገር ግን በዐይናችሁ ያለውን ምሰሶ ስለምን አትመለከቱም?

ወይም ወንድማችሁን ከዐይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትሉታላችሁ? እናም እነሆ በዐይናችሁ ምሰሶ አለ።

እናንተ ግብዞች አስቀድማችሁ በዐይናችሁ ያለውን ምሰሶ አውጡ፤ እናም ከዚያም በኋላ ከወንድማችሁ ዐይን ጉድፉን ታወጡ ዘንድ አጥርታችሁ ታያላችሁ።

በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ።

ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።

የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፣ እናም የሚፈልግም ያገኛል፤ እናም ለሚያንኳኩ ይከፈትላቸዋል።

ወይም ከእናንተ ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው ማነው?

ወይም ዓሳስ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋልን?

፲፩ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፣ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?

፲፪ ስለሆነም፣ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፣ ህግም ነቢያትም ይህ ነውና።

፲፫ በጠበበው ደጅ ግቡ፣ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፤ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙ ናቸው፤

፲፬ ምክንያቱም ወደ ህይወት የሚወስደው ደጁ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ስለሆነ፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።

፲፭ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ፣ ነገር ግን ውስጣቸው ነጣቂ ተኩላ ከሆኑ ከሀሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።

፲፮ ከፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን፣ ወይም ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?

፲፯ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፤ ክፉ ዛፍም መጥፎ ፍሬ ያፈራል።

፲፰ መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፣ ወይንም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬን ማፍራት አይቻለውም።

፲፱ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፣ ወደ እሳትም ይጣላል።

ስለዚህ፣ ከፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ።

፳፩ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።

፳፪ በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢትን አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል

፳፫ እናም ከቶ አላውቃችሁም፣ እናንተ አመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ አሳውቃቸዋለሁ።

፳፬ ስለዚህ፣ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ፣ ቤቱን በአለት ላይ እንደሰራ እንደ ጠቢብ ሰው አመሳስለዋለሁ—

፳፭ እናም ዝናብ ወረደና፣ የጥፋት ውሀም መጣ፤ እናም ነፋስ ነፈሰና፣ ቤቱን ገፋው፤ እናም በአለትም ላይ ስለተመሰረተ አልወደቀም

፳፮ እናም ይህንን ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ እንደሰራ ሰነፍ ሰው ይመሳሰላል—

፳፯ እናም ዝናቡ ወረደና፣ የጥፋት ውሀም መጣ፣ እናም ነፋሱ ነፈሰና፣ ቤቱን ገፋው፤ ወደቀና፣ አወዳደቁም ታላቅ ነበር።