ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፲፪


ምዕራፍ ፲፪

ኢየሱስ አስራ ሁለቱን ደቀመዛሙርት ጠራ እናም ስልጣንን ሰጣቸው—በተራራው ላይ እንዳደረገው ስብከት ለኔፋውያንም አደረገ—ብፅዕናን ተናገራቸው—ትምህርቱም የላቀ ነበር እናም ከሙሴ ህግም ቅድሚያ ያለው ነው—እርሱና አባቱ ፍፁም እንደሆኑ እነርሱም ፍጹም እንዲሆኑ ታዘዋል—ማቴዎስ ፭ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት ለኔፋውያንና፣ ለተጠሩት በተናገረበት ጊዜ፣ (የተጠሩት እናም ለማጥመቅ ኃይልንና ስልጣንን የተቀበሉት አስራ ሁለት ነበሩ) እናም እነሆ፣ እጁንም ወደ ህዝቡ ዘረጋና እንዲህ ሲል ጮኸ፥ እናንተን እንዲያስተምሩና የእናንተ አገልጋዮች እንዲሆኑ ከመካከላችሁ የመረጥኋቸውን የእነዚህን የአስራ ሁለቱን ቃላት በጥንቃቄ የምታዳምጡ ከሆነ የተባረካችሁ ናችሁ፤ እናም እነርሱ በውኃ ያጠምቋችሁ ዘንድ ስልጣንን ሰጥቻቸዋለሁ፤ በውኃም ከተጠመቃችሁ በኋላ፣ እነሆ፣ እኔ፣ በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ አጠምቃችኋለሁ፤ ስለዚህ እኔን ከተመለከታችሁና፣ እኔ መሆኔን ካወቃችሁ በኋላ በእኔ ካመናችሁና፣ ከተጠመቃችሁ እናንተ የተባረካችሁ ናችሁ።

እናም በድጋሚ፣ እናንተ እኔን ማየታችሁንና እኔ መሆኔን ማወቃችሁን በመመስከራችሁ በቃላችሁ ያመኑት ይበልጥ የተባረኩ ናቸው። አዎን፣ በቃላችሁ ያመኑት፣ እናም እራሳቸውን በጥልቅ ትህትና ያወረዱትና፣ የተጠመቁት የተባረኩ ናቸው፣ በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ ይጎበኛሉ፣ እናም ለኃጢአታቸው ስርየትን ይቀበላሉና።

አዎን፣ በመንፈስ ድሆች የሆኑ ወደ እኔም የሚመጡ ብፁአን ናቸው፣ መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።

እናም ደግሞ የሚያዝኑ ብፁዐን ናቸው፣ መፅናናትን ያገኛሉና።

እናም የዋሆች ብፁአን ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና።

እናም ፅድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ሁሉ ብፁአን ናቸው፣ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላሉና።

እናም ምህረትን የሚያደርጉ ብፁአን ናቸው፣ ምህረትን ያገኛሉና።

እናም በልባቸው ንፁሃን የሆኑ ሁሉ ብፁአን ናቸው፣ እግዚአብሔርን ያዩታልና

እናም የሚያስተራርቁ ሁሉ ብፁአን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።

እናም ስለስሜ የሚሰደዱ ሁሉ ብፁአን ናቸው፣ መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።

፲፩ እናም ሰዎች ሲሰድቡአችሁና፣ ሲያሳድዱአችሁና በሃሰትም ሁሉንም ዐይነት ክፋት በእናንተ ላይ ስለእኔ ሲናገሩባችሁ፣ እናንተ ብፁአን ናችሁ፤

፲፪ ታላቅ ደስታም ይኖራችኋል እናም እጅግ ትደሰታላችሁ፣ በሰማይም ዋጋችሁ ትልቅ ይሆናልና፤ ከእናንተም በፊት የነበሩትን ነቢያት እንዲሁም አሳድደዋቸዋልና።

፲፫ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተ የምድር ጨው እንድትሆኑ እሰጣችኋለሁ፤ ነገር ግን ጨው ጣዕሙን ካጣ ምድር እንዴት ትጣፈጣለች? ነገር ግን ለመጣል፣ እናም በሰዎች እግር በመረገጥ እንጂ ጨውም ከዚያን ጊዜ በኋላ ከንቱ ይሆናል።

፲፬ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ የዚህ ህዝብ ብርሃን እንድትሆኑ አሰጣችኋለሁ። በኮረብታ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።

፲፭ እነሆ፣ ሰዎች ሻማ አብርተው ከዕንቅቡ በታች ያደርጉታልን? አይደለም፣ ነገር ግን በሻማ ማብሪያው ላይ ያደርጉታል፣ እናም በቤቱ ውስጥ ላሉት ሁሉም ብርሃንን ይሰጣል፤

፲፮ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች መልካም ስራዎቻችሁን ተመልክተው፣ እናም በሰማይ ያለው አባታችሁን ያከብሩ ዘንድ ብርሃናችሁ በፊታቸው ሁሉ ይብራ።

፲፯ ህጉን ወይንም ነቢያትን ልሽር እንደመጣሁ አታስቡ። ለመሻር ሳይሆን የመጣሁት ልፈፅመው ነው፤

፲፰ በእውነት እንዲህ እላችኋለሁ፣ ከሕግ አንዲት የወጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፣ ነገር ግን በእኔ ሁሉም ተፈፅሟል።

፲፱ እናም እነሆ፣ በእኔ እንድታምኑ ዘንድና፣ ከኃጢአቶቻችሁ ንስሀ እንድትገቡ ዘንድ፣ እናም በተሰበረ ልብ እና በተዋረደ መንፈስ ወደ እኔ ትመጡ ዘንድ፣ የአባቴን ህግና ትዕዛዛትን ሰጥቻችኋለሁ። እነሆ፣ ትዕዛዛቱ በፊታችሁ አሉ፣ እናም ህጉም ተፈፅሟል።

ስለዚህ ወደ እኔ ኑ፣ እናም ዳኑ፤ እውነት እላችኋለሁና፣ በዚህ ጊዜ ያዘዝኳችሁን ትዕዛዛት ካልጠበቃችሁ በቀር፣ በምንም ምክንያት ወደ መንግስተ ሰማያት አትገቡም።

፳፩ በጥንት ጊዜም በነበሩት አትግደሉ ሲባል ሰምታችኋል፤ እናም ደግሞ በእናንተ ፊትም ተፅፎአል፣ እና የገደለም በእግዚአብሔር ፍርድ አደጋ ላይ ይሆናል፤

፳፪ ነገር ግን እንዲህ እላችኋለሁ፣ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ በእግዚአብሔር ቅጣት አደጋ ላይ ይሆናል። እናም ወንድሙን ጨርቃም ብሎ የሚናገር ቢኖር በምክሩ አደጋ ላይ ነው፤ እናም ሞኝ ብሎ የሚናገርም በገሃነሙ እሳት አደጋ ላይ ነው።

፳፫ ስለዚህ ወደእኔ ብትመጡ ወይንም ለመምጣት የምትፈልጉ ከሆናችሁ፣ እናም ወንድማችሁ በእናንተ ላይ አንድ ነገር እንዳለው ካስታወሳችሁ፤

፳፬ ወደ ወንድማችሁም ሂዱ፣ እናም በመጀመሪያ ከወንድማችሁ ጋር ተስማሙ፤ እናም በልባችሁ ሙሉ ዓላማ ወደእኔ ኑ፣ እናም እኔ እቀበላችኋለሁ።

፳፭ ከጠላታችሁ ጋር በአንድ መንገድ ስትሆኑ ፈጥናችሁ ተስማሙ፣ ያለበለዚያ ብልጫ እንዳያገኝባችሁ፣ እናም ወደ ወህኒ እንዳትጣሉ።

፳፮ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ያለባችሁን ሰኒን እስከምትከፍሉ ከዚያ በምንም መንገድ አትወጡም። እናም በወህኒ በሆናችሁ ጊዜ አንድ ሰኒን እንኳን ለመክፈል ትችላላችሁን? እውነት እላችኋለሁ አትችሉም።

፳፯ እነሆ፣ አታመንዝር ተብሎ በጥንቶቹ ተጽፏል፤

፳፰ ነገር ግን እንዲህ እላችኋለሁ፣ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።

፳፱ እነሆ፣ እናንተ ከእነዚህ ነገሮች ማንኛውም ወደ ልባችሁ እንዲገባ አትፍቀዱ ትዕዛዛትን ሰጥቻችኋለሁ፤

ወደገሃነም ከምትጣሉ ይልቅ በእነዚህም ነገሮች ራሳችሁን ብትክዱ፣ መስቀላችሁንም ብትሽከሙ የተሻለ ይሆናል።

፴፩ ሚስቱን የሚፈታ ህጋዊ የፍቺ ማስረጃ ይስጣት የሚል ተፅፏል።

፴፪ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ በማመንዘር ምክንያት ካልሆነ በቀር ሚስቱን የሚፈታ ቢኖር፣ ዝሙት እንድትፈጽም ያደርጋታል ማለት ነው፤ እናም የተፈታችውን የሚያገባ ዝሙትን ፈፅሟል።

፴፫ እናም በድጋሚ በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ እንደተባለ ሰምታችኋል፤

፴፬ ነገር ግን እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ በፍፁም አትማሉ፤ የአምላክ ዙፋን ነውና፣ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤

፴፭ ምድርም የእግሩ መረገጫ ናትና በእርሷም አትማሉ፤

፴፮ በራሳችሁም አትማሉ፣ ምክንያቱም ከራሳችሁ አንዲት ፀጉር እንኳን ጥቁር ወይንም ነጭ ለማድረግ አትችሉምና፤

፴፯ ነገር ግን ቃላችሁ አዎን፣ አዎን፣ አይደለም፣ አይደለም ይሁን፤ ከዚህ የበለጠ የተባለም ከክፉ ነውና።

፴፰ እናም እነሆ፣ ለዐይን ዐይን፣ እንዲሁም ለጥርስ ጥርስ ተብሎ ተፅፏል፤

፴፱ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ከመጥፎ ጋር አትታገሉ፣ ነገር ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት

እናም ማንኛውም ሰው በህግ ፊት ቢያቀርባችሁ፣ እናም እጀጠባባችሁን ቢወስድ መጎናፀፊያችሁን ደግሞ እንዲወስድ ፍቀዱለት፤

፵፩ እናም ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ።

፵፪ ለሚጠይቅህ ስጠው፣ እናም ከአንተ ለመበደር የሚፈልግንም አትከልክልው።

፵፫ እናም እነሆ ደግሞ ባልንጀራህን ውደድና ጠላቶችህን ጥላ ተብሎ ተፅፏል፤

፵፬ ነገር ግን እነሆ፣ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሟችሁንም ባርኩ፤ ለሚጠሏችሁም መልካምን አድርጉ፣ እናም በከንቱ የሚነቅፉአችሁንና የሚያሳድዱአችሁን ጸልዩላቸው እላችኋለሁ።

፵፭ በሰማይ ያለው የአባታችሁ ልጆች እንድትሆኑም፤ ፀሀዩንም ለመጥፎ እና ለመልካም ሰዎች እንድትወጣ ያደርጋልና።

፵፮ ስለዚህ በጥንት ጊዜ በህጉ ስር የነበሩትም እነዚያ ነገሮች፣ በእኔ ሁሉም ተፈፅመዋል።

፵፯ በጥንት የነበሩት ነገሮች ተፈፅመዋል፣ እናም ሁሉም ነገሮች አዲስ ሆነዋል።

፵፰ ስለዚህ እንደእኔ ወይንም በሰማይ እንዳለው ፍፁም እንደሆነው አባታችሁ ፍፁም እንድትሆኑ እፈልጋችኋለሁ።