ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፴፩


ምዕራፍ ፴፩

ኔፊ ክርስቶስ ለምን እንደተጠመቀ ይናገራል—ሰዎች ለመዳን ክርስቶስን መከተል፣ መጠመቅ፣ መንፈስ ቅዱስን መቀበል እናም እስከመጨረሻው መፅናት ይኖርባቸዋል—ንስሀ መግባትና ጥምቀት የጠባቡና ቀጭኑ ጎዳና መግቢያ ናቸው—የዘለዓለም ህይወት ከጥምቀት በኋላ ትዕዛዛትን ለሚጠብቁት ይመጣል። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እኔ ኔፊ፣ ለእናንተ ትንቢት መናገሬን እጨርሳለሁ። እናም በእርግጥ መምጣት አለበት ብዬ ከማውቀው ጥቂት ነገሮችን በስተቀር መፃፍ አልችልም፤ የወንድሜ ያዕቆብንም ጥቂት ቃላት ብቻ ነው መፃፍ የምችለው።

ስለሆነም፣ እኔ የፃፍኳቸው ነገሮች ስለክርስቶስ ትምህርት መናገር ካለብኝ በስተቀር ለእኔ በቂ ናቸው፤ ስለሆነም፣ በትንቢቴ ግልፅነት መሰረት በግልፅ እናገራችኋለሁ።

ነፍሴ በግልፅነት ትደሰታለችና፤ ጌታ እግዚአብሔርም በሰዎች ልጆች መካከል የሚሰራው በእንዲህ ያለ ሁኔታ ነውና። ጌታ እግዚአብሔር ለመረዳት ብርሃንን ይሰጣልና፤ ለሰዎችም በሚረዱት፣ እንደ ቋንቋቸው ይናገራቸዋልና።

ስለሆነም፣ እናንተ የተናገርኳችሁ የዓለምን ኃጢያት የሚያስወግደውን የእግዚአብሔርን በግ የሚያጠምቀውን ነቢይ በተመለከተ ጌታ ያሳየኝን በተመለከተ ያሳየኝን እንድታስታውሱ እፈልጋለሁ።

እናም አሁን የእግዚአብሔር በግ፣ ቅዱስ ሆኖ፣ ፅድቅን ሁሉ ለመፈፀም በውሃ መጠመቅ ካስፈለገው፣ አቤቱ ቅዱስ ያልሆንነው፣ አዎን፣ እኛ በውሃ እንኳን መጠመቅ ምን ያህል ያስፈልገናል!

እናም አሁን፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እጠይቃችኋለሁ—የእግዚአብሔር በግ በውሃ በመጠመቅ ፅድቅን ሁሉ የፈፀመው እንዴት ነበር?

ቅዱስ እንደነበር አታውቁምን? ነገር ግን ቅዱስም እንኳን ቢሆን፣ በስጋ መሰረት ለሰው ልጆች በአብ ፊት እራሱን እንዳዋረደ አሳይቷል፣ እናም ትዕዛዛቱን በመጠበቅ ለእርሱ ታዛዥ መሆኑን ለአባቱ መስክሯል።

ስለሆነም፣ እርሱ በውሃ ከተጠመቀ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል በላዩ ላይ አረፈ።

እናም እንደገና፣ እርሱ በፊታቸው ምሳሌ በመሆን፣ ለሰዎች ልጆች የጎዳናውን ቀጥተኝነትና፣ እነርሱ በዚያ መግባት ያለባቸው በሩን ጥበት አሳይቷቸዋል።

እናም ለሰዎች ልጆች፣ እኔን ተከተሉኝ አለ። ስለዚህ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ የአብን ትዕዛዛት ለመጠበቅ ፈቃደኞች ከመሆን በስተቀር ኢየሱስን ልንከተለው እንችላለን?

፲፩ እናም አብ እንዲህ ይላል፥ ንስሀ ግቡ፣ ንስሀ ግቡ፣ እናም በተወደደው ልጄ ስም ተጠመቁ።

፲፪ እናም ደግሞ፣ የወልድ ድምፅ ወደ እኔ መጥቶ እንዲህ አለኝ፥ በስሜ የተጠመቀ፣ አብ እንደ እኔ መንፈስ ቅዱስን ይሰጠዋል፤ ስለሆነም፣ ተከተሉኝ፣ እናም እኔ ስሰራ ያያችሁትን ስሩ።

፲፫ ስለዚህ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ በሙሉ ልባችሁ አላማ፣ በእግዚአብሔር ፊት ባለማስመሰልና ያለግብዝነት፣ ነገር ግን በእውነት ፍላጎት፣ ለኃጢአታችሁ ንስሀ በመግባት፣ በጥምቀት የክርስቶስን ስም ለእራሳችሁ መውሰዳችሁን ለአብ በመመስከር ወልድን ብትከተሉ—አዎን፣ እንደቃሉ ጌታችሁንና አዳኛችሁን ወደ ውኃው ብትከተሉ፣ እነሆ፣ ከዚያም መንፈስ ቅዱስን ትቀበላላችሁ፤ አዎን፣ የእሳትና የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ይመጣል፤ እናም ከዚያ በኋላ በመላዕክት ልሳን መናገርና ለእስራኤል ቅዱስም በምስጋና መጮህ ትችላላችሁ።

፲፬ ነገር ግን እነሆ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ የወልድ ድምፅ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፥ ለኃጢአታችሁ ንስሀ ከገባችሁና፣ በውኃ በመጠመቅ ትዕዛዛቴን ለመጠበቅ ፈቃደኛ እንደሆናችሁ ለአብ ከመሰከራችሁ፣ እና የእሳትንና የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት በመቀበላችሁ፣ እናም በአዲስ ልሳን፣ አዎን፣ እንዲያውም በመላዕክት ልሳንም ለመናገር ከቻላችሁ በኋላ፣ ከዚህም በኋላ የምትክዱኝ ከሆነ፣ ፈፅሞ ባታውቁኝ ምንኛ ይሻላችሁ ነበር።

፲፭ እናም ከአብ እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ፥ አዎን፣ የተወደደው ልጄ ቃላት እውነትና የታመኑ ናቸው። እስከመጨረሻው የሚፀና እርሱ ይድናል።

፲፮ እናም አሁን፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ የህያው እግዚአብሔርን ልጅ ምሳሌን በመከተል ሰው እስከመጨረሻው የማይፀና ከሆነ፣ መዳን እንደማይችል በዚህ አውቃለሁ።

፲፯ ስለዚህ፣ ጌታችሁና አዳኛችሁ ሲያደርግ እንዳየሁ የነገርኳችሁን ነገሮች አድርጉ፤ መግቢያችሁን ታውቁት ዘንድ፣ ለዚህም ነው እነዚህን ነገሮች የታዩኝ። የምትገቡበትም በር ንስሀና የውኃ ጥምቀት ነው፤ እና ከእዚያም የኃጢአታችሁ ስርየት በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ ይመጣሉ።

፲፰ እና ከእዚያም እናንተ ወደ ዘለዓለማዊው ህይወት በሚመራው በዚህ በቀጭኑና ጠባቡ ጎዳና ላይ ናችሁ፤ አዎን፣ በበሩ ገብታችኋል፤ በአብና በወልድ ትዕዛዛት መሰረትም አድርጋችኋል፤ እናም በትክክለኛው መንገድ ከገባችሁ ትቀበላላችሁ ያለውን የተስፋውንም ቃል በመፈፀም፣ ስለአብና ስለወልድ የሚመሰክረውን መንፈስ ቅዱስ ተቀብላችኋል።

፲፱ እናም አሁን፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ በጠባቡና በቀጭኑ ጎዳና ከገባችሁ በኋላ፣ ሁሉ ተደርጓልን? ብዬ እጠይቃችኋለሁ። እነሆ፣ አይደለም፣ እላችኋለሁ፤ በክርስቶስ ቃል በማይናወጥ እምነት ለማዳን ኃያል በሆነው መልካም ስራ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ባይሆን ኖሮ እስከዚህ አትመጡም ነበር።

ስለሆነም ፍጹም የሆነ የተስፋ ብርሃን፣ እናም የእግዚአብሔርና የሰዎች ሁሉ ፍቅር እየኖራችሁ በክርስቶስ ባላችሁ ፅኑነት መቀጠል አለባችሁ። ስለሆነም አብም፣ የክርስቶስን ቃል በመመገብ፣ እናም እስከመጨረሻው በመፅናት የምትቀጥሉ ከሆነ፣ እነሆ አብ እንዲህ ይላል፥ የዘለዓለም ህይወት ይኖራችኋል።

፳፩ እናም አሁን፣ እነሆ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ መንገዱ ይህ ነው፤ ሰው በእግዚአብሔር መንግስት መዳን የሚችልበት ከሰማይ በታች የተሰጠ ሌላ ምንም መንገድም ሆነ ስም የለምና። እናም አሁን፣ እነሆ፣ ይህ የክርስቶስ ትምህርትና፣ መጨረሻ የሌለው አንድ አምላክየአብ፣ የወልድና፣ የመንፈስ ቅዱስ ብቸኛውና እውነተኛው ትምህርት ነው። አሜን።