ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፲፩


ምዕራፍ ፲፩

ያዕቆብ መድኃኒቱን አየ—የሙሴ ህግ የክርስቶስ ምሳሌዎች ናቸው እናም የእርሱን መምጣት ያረጋግጣል። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን፣ ያዕቆብ በዚያን ጊዜ ለህዝቤ ብዙ ነገሮችን ተናገረ፤ ሆኖም እነዚህን ነገሮች ብቻ እንዲፃፉ አደረግሁ፣ ምክንያቱም እኔ የፃፍኳቸው ነገሮች ይበቁኛልና።

እናም አሁን እኔ ኔፊ፣ የኢሳይያስን ቃል በተጨማሪ እፅፋለሁ፣ ምክንያቱም በእርሱ ቃል ነፍሴ ትደሰታለች። ቃላቱን ለህዝቤ አመሳስልላቸዋለሁ፣ እናም ለልጆቼ ሁሉ አሰራጫቸዋለሁ፣ ምክንያቱም እርሱ በእውነት መድኃኒቴን፣ እኔ እንዳየሁት፣ አይቶታልና።

እናም እኔ እንዳየሁት ወንድሜ ያዕቆብም ደግሞ አይቶታል፤ ስለዚህ፣ ቃሌ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ የእነርሱን ቃል ለልጆቼ እልካለሁ። ስለዚህ፣ እግዚአብሔር በሶስት ሰዎች ቃል ቃሌን አፀናለሁ ብሏል። ይሁን እንጂ፣ እግዚአብሔር የበለጡ ምስክሮችን ይልካል፣ እናም ቃሉን በሙሉ ያረጋግጣል።

እነሆ፣ የሚመጣውን ክርስቶስ እውነታ ለህዝቦቼ በማረጋገጥ ነፍሴ ትደሰታለች፤ ለዚህም ምክንያት ነው የሙሴ ህግ የተሰጠው፤ እናም ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ ለሰዎች በእግዚአብሔር የተሰጡት ነገሮች ሁሉ የእርሱ ምሳሌዎች ናቸው።

እናም ደግሞ ነፍሴ ጌታ ለአባቶቻችን በገባው ቃል ኪዳን ትደሰታለች፤ አዎን፣ በፀጋውና በፍርዱና፤ በሀይሉ እና በምህረቱ፣ በታላቁና ከሞት በሚያድነው ዘለአለማዊው እቅዱ፣ ነፍሴ ትደሰታለች።

እናም ክርስቶስ ካልመጣ በስተቀር ሁሉም ሰው እንደሚጠፋ ለህዝቤ በማረጋገጤ ነፍሴ ትደሰታለች።

ክርስቶስ ከሌለ እግዚአብሔር አይኖርምና፤ እናም እግዚአብሔር ከሌለ እኛም አንኖርም፣ ምክንያቱም ምንም ፍጡር ሊኖር አይችልምና። ነገር ግን እግዚአብሔር አለ፣ እርሱም ክርስቶስ ነው፣ እናም በዘመኑ ፍፃሜ ይመጣል።

እናም አሁን ከህዝቤ ማንም ይህንን ቃል የሚያይ ልብን ከፍ እንዲያደርጉና ለሰዎች ሁሉ ይደሰቱ ዘንድ፣ ከኢሳይያስ ቃል በጥቂቱ እፅፋለሁ። አሁን ቃሉ ይህ ነው፣ እናም በራሳችሁና በሁሉም ሰዎች አነፃፅሯቸው።