ቅዱሳት መጻህፍት
፩ ኔፊ ፭


ምዕራፍ ፭

ሳርያ በሌሂ ላይ አጉረመረመች—በወንዶች ልጆቻቸው መመለስ ሁለቱም ተደሰቱ—መስዋዕትም አቀረቡ—የነሀስ ሰሌዳዎቹ የሙሴን እና የነቢያትን ፅህፈቶች ይዘዋል—ሰሌዳዎቹ ሌሂ ከዮሴፍ ትውልድ መሆኑን ያሳያሉ—ሌሂ ስለዘሮቹና ሰሌዳዎቹን ስለመጠበቅ ተነበየ። ፮፻–፭፻፺፪ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ ወደ አባታችን ወደ ምድረበዳ ከመጣን በኋላ እነሆ እርሱ በደስታ ተሞላ፣ እንዲሁም እናቴ ሳርያም እጅግ ተደሰተች፣ በእውነት በእኛ ምክንያት አዝና ነበርና።

እርሷም እኛ በምድረበዳ ውስጥ እንደጠፋን አስባ ነበር፤ እና እርሷም በአባቴ ላይ እርሱ ባለራዕይ እንደሆነ በመንገር ቅሬታዋን ገልጻ ነበር፤ እንዲህም አለች፥ እነሆ ከርስት ምድራችን መርተህ አውጥተንሀል፣ ወንዶች ልጆቼም ከእንግዲህ የሉም፣ እናም እኛም በምድረበዳ ውስጥ እንጠፋለን።

በእንዲህ ዓይነት አነጋገር ነበር እናቴ በአባቴ ላይ ቅሬታዋን የገለጸችው።

እናም እንዲህ ሆነ አባቴ እንዲህ ብሎ ተናገራት፥ ባለራዕይ ሰው መሆኔን አውቃለሁ፣ የእግዚአብሔርን ነገሮች በራዕይ ባላይ ኖሮ የእግዚአብሔርን ቸርነት አላውቅም ነበር፣ ነገር ግን በኢየሩሳሌም እቆይ ነበር፣ እና ከወንድሞቼ ጋር እጠፋ ነበር።

ነገር ግን እነሆ የቃልኪዳኑን ምድር አገኛለሁ፣ በነዚህም ነገሮች እደሰታለሁ፣ አዎን፣ ጌታ የእኔን ወንዶች ልጆች ከላባን እጅ ነፃ እንደሚያወጣቸው እንዲሁም ወደ እኛ ወደ ምድረበዳው ዳግመኛ እንደሚያመጣቸው አውቃለሁ

እናም በዚህ ዓይነት አነጋገር ነበር አባቴ ሌሂ እኛ በምድረበዳ ውስጥ ወደ ኢየሩሳሌም ምድር፣ የአይሁዶችን መዝገብ ለማግኘት ስንጓዝ፣ እናቴ ሳርያን እኛን በተመለከተ ያፅናናት።

እናም እኛ ወደ አባቴ ድንኳን ስንመለስ እነሆ የእነርሱ ደስታ የተሟላ ነበር፣ እናቴም ተፅናናች።

እናም እርሷ እንዲህ በማለት ተናገረች፥ ጌታ ባለቤቴን ወደ ምድረበዳው እንዲሸሽ እንዳዘዘው አሁን በእርግጥ አወቅሁ፣ አዎን እንዲሁም ደግሞ ጌታ ወንዶች ልጆቼን እንደጠበቀልኝ እንዲሁም ከላባን እጆች ነፃ እንዳወጣልኝና፣ ጌታ ያዘዛቸውን ነገር ማከናወን እንዲችሉ ኃይልን እንደሰጣቸው በእርግጥ አወቅሁ። በእንዲህ ዓይነት ነበር እርሷ የተናገረችው።

እናም እንዲህ ሆነ እነሱ እጅግ ተደሰቱ፣ መስዋዕት አቀረቡ፣ የሚቃጠል መስዋዕት ለጌታ አቀረቡ፣ እናም የእስራኤል አምላክንም አመሰገኑ

እናም ለእስራኤል አምላክ ምስጋናውን ካቀረቡ በኋላ፣ አባቴ ሌሂ በነሀስ ሰሌዳዎች ላይ የተቀረፀውን መዝገብ ወሰደው፣ እናም ከመጀመሪያ ጀምሮ መረመራቸው።

፲፩ እናም እርሱም እነርሱ ስለዓለም አፈጣጠር፣ እንዲሁም የመጀመሪያ የእኛ ወላጆች የሆኑትን የአዳምና የሔዋን ታሪክ የሚገልጹትን አምስቱን የሙሴ መፅሐፍት እንደያዙ አየ፤

፲፪ እናም ደግሞ የአይሁዶችን መዝገብ፣ ከመጀመሪያው እስከ የይሁዳ ንጉስ ሴዴቅያስ የንግሥ ዓምት መጀመሪያ ድረስ ይዘው ነበር፤

፲፫ እናም ደግሞ የቅዱሳን ነቢያት ትንቢቶች፣ ከመጀመሪያ እስከ ሴዴቅያስ የንግስ መጀመሪያ ድረስ እንዲሁም ደግሞ በኤርምያስ አፍ የተነገሩ ብዙ ትንቢቶችንም ይዘው ነበር።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ አባቴ ሌሂ ደግሞ በነሀስ ሰሌዳዎቹ ላይ የአባቶቹን የትውልድ ሐረግ ታሪክ አገኘ፤ ስለዚህ እርሱ ከዮሴፍ ትውልድ እንደሆነ አወቀ፤ አዎን፣ በእርግጥ ዮሴፍ የያዕቆብ ልጅ የሆነው ወደግብፅ የተሸጠው፣ እናም እርሱ አባቱን ያዕቆብንና ሁሉንም ቤተሰዎቹን በረሃብ ከመጥፋት ያድናቸው ዘንድ በጌታ እጅ የተጠበቀው ነበር።

፲፭ እናም እነርሱ ደግሞ ከምርኮ ከግብፅ ምድር ከዚህ በፊት በጠበቃቸው አምላክ ተመርተው የዳኑ ናቸው።

፲፮ እናም እንደዚህ ነበር አባቴ፣ ሌሂ፣ የአባቶቹን የትውልድ ሐረግ ያገኘው። ላባንም የዮሴፍ ትውልድ ነበር፣ ስለዚህ እርሱና አባቶቹ መዝገቦችን ጠብቀው አቆዩ።

፲፯ እናም አሁን አባቴ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ባየ ጊዜ፣ በመንፈስ ተሞላና፣ ስለዘሮቹ መተንበይ ጀመረ—

፲፰ እነዚህ የነሀስ ሰሌዳዎች የእርሱ ዘሮች ለሆኑት ለሁሉም ሀገሮች፣ ነገዶች፣ ቋንቋዎችና ህዝቦች ሁሉ መሄድ ይኖርባቸዋል።

፲፱ ስለዚህ እነዚህ የነሀስ ሰሌዳዎች በፍፁም መጥፋትም ሆነ ከጊዜ ብዛት ሊደበዝዙም አይገባም አለ። እናም ዘሮቹን በተመለከተ ብዙ ነገሮችን ተነበየ።

እናም እንዲህ ሆነ እስከአሁን እኔና አባቴ ጌታ ያዘዘንን ትዕዛዛት ጠበቅን።

፳፩ እናም እኛ ጌታ እንድናገኝ ያዘዘንን መዝገቦች አግኝተናልና መርምረናቸዋል፣ እነሱም ጠቃሚ እንደሆኑ፣ አዎን፣ የጌታን ትዕዛዛት ለልጆቻችን ማቆየት እስኪቻለን ያህል ለእኛ ትልቅ ዋጋ ያላቸው እንደሆኑ አግኝተናቸዋል።

፳፪ ስለዚህ እኛ ወደ ቃልኪዳኑ ምድር በምድረበዳ ውስጥ ስንጓዝ ከእኛ ጋር ይዘናቸው እንሄድ ዘንድ የጌታ ጥበብ ነበር።