ቅዱሳት መጻህፍት
፩ ኔፊ ፲፯


ምዕራፍ ፲፯

ኔፊ መርከብ እንዲሰራ ታዘዘ—ወንድሞቹ ተቃወሙት—ከእስራኤል ጋር እግዚአብሔር ያደረገውን ታሪክ በመንገር አበረታታቸው—ኔፊ በእግዚእብሔር ኃይል ተሞላ—ወንድሞቹ እንዳይነኩት ተከለከሉ፣ አለበለዚያ ልክ እንደደረቀ ሸንበቆ ይኮማተራሉ። ከ፭፻፺፪–፭፻፺፩ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ እንደገና በምድረበዳ ውስጥ ጉዟችንን አደረግን፤ እናም ከዚያ ጊዜ በኋላ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ተጓዝን። በምድረበዳው ውስጥም በብዙ ስቃይ ተገፋን፤ ሴቶቻችንም በምድረበዳ ውስጥ ልጆችን ወለዱ።

እናም የጌታ በረከት በእኛ ላይ ታላቅ ስለነበር በምድረበዳ ውስጥ ለመኖር ስንል ጥሬ ስጋ ብንበላም ሴቶቻችን ልጆቻቸውን በበቂ ሁኔታ አጠቡአቸው፣ እነርሱም ጠንካራ አዎን፣ ልክ እንደወንዶችም ነበሩ፣ ካለምንም ማጉረምረም ጉዞአቸውን መታገስ ጀመሩ።

በዚህም የእግዚአብሔር ትዕዛዛት መፈፀም እንዳለባቸው ተመለከትን። እናም የሰዎች ልጆች የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ከጠበቁ እርሱ ይመግባቸዋል፣ ያበረታታቸዋልም፣ እንዲሁም እርሱ ያዘዛቸውን ነገር መፈፀም የሚችሉበትን ዘዴ ያቀርብላቸዋል፤ ስለዚህ እኛ በምድረበዳ በተቀመጥን ጊዜ እርሱ የሚያስፈልጉንን ነገሮች አቀረበልን

እናም እኛ ለብዙ አመታት፣ አዎን፣ ለስምንት ዓመታትም በምድረበዳ ውስጥ ተቀመጥን።

እናም በበርካታ ፍራፍሬዎቹና በዱር ማሩ ምክንያት ለጋስ ብለን ወደጠራነው ምድር መጣን፤ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በጌታ የተዘጋጁልን እንዳንጠፋ ነበሩ። እናም ባህርን ተመለከትን፣ ኢሬአንቱም ብለን ጠራነው፣ ትርጓሜውም ብዙ ውኃዎች ማለት ነው።

እናም እንዲህ ሆነ በባህሩ ዳርቻ ድንኳኖቻችንን ተከልን፤ እናም በብዙ መከራና ችግሮች ብንሰቃይም፣ አዎን፣ ብዙ ሆነው ሁሉንም እንኳን መፃፍ ባንችልም፣ ወደ ባህሩ ዳርቻ ስንመጣ እጅግ ደስተኞች ነበርን፤ እናም በብዙ ፍሬዎቹ ምክንያት ቦታውን ለጋስ ብለን ጠራነው።

እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ፣ በለጋሱ ምድር ለብዙ ቀናት ከቆየሁ በኋላ የጌታ ድምፅ ወደእኔ መጥቶ እንዲህ አለኝ—ተነስ እናም ወደ ተራራው ውጣ። እናም እንዲህ ሆነ ተነስቼ ወደ ተራራው ወጣሁ፣ እናም ወደጌታ ጮህኩ።

እናም እንዲህ ሆነ ጌታ እንዲህ ሲል ተናገረኝ—ህዝብህን በዚህ ውኃ ላይ አሻግረው ዘንድ እኔ በማሳይህ ቅርፅና ዘዴ መርከብ ስራ።

እናም አልኩ—ጌታ ሆይ፣ መርከቡን አንተ ባሳየኸኝ ቅርፅና ዘዴ ለመስራት መሳሪያዎችን እሰራበት እንድችል ዘንድ የማቀልጠው የብረት አፈር ለማግኘት ወዴት ልሂድ?

እናም እንዲህ ሆነ መሳሪያዎችን እሰራበት ዘንድ የብረት አፈሩን ለማግኘት ወዴት መሄድ እንዳለብኝ ጌታ ነገረኝ።

፲፩ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ እሳት ለማቀጣጠል ከዱር እንስሳት ቆዳ ወናፍ ሰራሁ፤ እናም እሳቱን ለማቀጣጠል የምችልበት ወናፉን ከሰራሁ በኋላ፣ እሳት አገኝ ዘንድ ሁለት ድንጋዮችን በአንድ ላይ አጋጨሁ።

፲፪ በምድረበዳ ውስጥ በምንጓዝበት ከዚህ ጊዜ በፊት ጌታ ይህንን ያህል እሳት እንድናቀጣጥል አልፈቀደም ነበር፤ እንዲህም አለ—ምግባችሁን እኔ ስለማጣፍጥላችሁ ይህን ማብሰል አያስፈልጋችሁም፤

፲፫ እናም በምድረበዳ ውስጥ እኔ ብርሃን እሆናችኋለሁ፤ እናም ትዕዛዛቴን ከጠበቃችሁ መንገዱን በፊታችሁ አዘጋጅላችኋለሁ፤ ስለዚህ ትዕዛዛቴን እስከጠበቃችሁ ድረስ ወደ ቃልኪዳኑ ምድር ትመራላችሁ፤ እናም የተመራችሁት በእኔ እንደሆነም ታውቃላችሁ

፲፬ አዎን፣ እናም ደግሞ ጌታ እንዲህ አለ—ወደ ቃልኪዳኑ ምድር ከደረሳችሁ በኋላ፣ እኔ ጌታ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ፤ እናም እኔ ጌታ ከጥፋት አዳንኳችሁ፤ አዎን ከኢየሩሳሌም ምድርም አወጣኋችሁ።

፲፭ ስለዚህ እኔ ኔፊ የጌታን ትዕዛዛት ለመጠበቅ ተጋሁ፣ እናም ወንድሞቼን ታማኝና ትጉ እንዲሆኑ አበረታታኋቸው።

፲፮ እናም እንዲህ ሆነ ከድንጋይ ባቀለጥኩት የብረት አፈር መሳሪያዎችን ሰራሁ።

፲፯ እናም ወንድሞቼ መርከብ ለመስራት ዕቅዴን ባዩ ጊዜ በእኔ ላይ እንዲህ ብለው ማጉረምረም ጀመሩ፥ ወንድማችን ሞኝ ነው፣ መርከብ ለመስራት ያስባልና፤ አዎን እናም ደግሞ ይህንን ታላቅ ውሃዎች ማቋረጥ ይችላል ብሎ ያስባል።

፲፰ እናም ወንድሞቼ በእኔ ላይ ተማረሩ፣ እናም ለመስራት አልፈለጉም ነበር፣ ምክንያቱም እኔ መርከብ መስራት በመቻሌ እምነት አልነበራቸውም፤ እናም በጌታ ታዝዤ እንደነበርኩም አላመኑም ነበርና።

፲፱ እናም አሁን እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ በልባቸው ጠጣርነት ምክንያት እጅግ አዝኜ ነበር፤ እናም አሁን ማዘኔን በተመለከቱ ጊዜ በልባቸው ደስተኞች ነበሩ፣ እንዲህም ሲሉ በእኔ ላይ ተሳለቁ፥ መርከብ መስራት እንደማትችል እናውቃለን፣ ምክንያቱም ሚዛናዊነት እንደሌለህ እናውቃለን፤ ስለዚህ አንተ እንደዚህ ያለ ታላቅ ስራ ለማከናወን አትችልም።

እና አንተ ልክ በከንቱ የልቡ ሀሳብ እንደተሳሳተ እንደ አባታችን ነህ፤ አዎን፣ እርሱ ከኢየሩሳሌም ምድር መርቶ አስወጣን፤ እናም በምድረበዳው ውስጥ ለእነዚህ በርካታ ዓመታት ተንከራተትን፤ እናም ሴቶቻችንም እርጉዝ በነበሩበት ጊዜ ለፉ፣ እናም በምድረበዳ ውስጥ ልጆችን ወለዱ፣ እናም ከሞት በስተቀር በሁሉም ነገሮች ተሰቃዩ፤ እናም በእነዚህ ነገሮች ከመሰቃየት ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ ቢሞቱ ይሻል ነበር።

፳፩ እነሆ በንብረታችን እና በውርስ ምድራችን ደስተኞች መሆን፣ አዎን እንዲሁም በሀሴት ልንኖር፣ በምንችልባቸው በእነዚህ በርካታ ዓመታት በሙሉ በምድረበዳ ተሰቃየን።

፳፪ እናም በኢየሩሳሌም ምድር የነበሩ ሕዝቦች ፃድቅ ሕዝቦች እንደነበሩ እናውቃለን፤ ምክንያቱም እነርሱ የጌታን ህግና ውሳኔ እንዲሁም በሙሴ ህግ መሰረት ሁሉንም ትዕዛዛት ጠብቀዋልና፤ ስለዚህ እነሱ ፃድቅ ሕዝቦች እንደሆኑ አወቅን፤ እናም አባታችን ፈረደባቸው፣ እናም እኛ ቃላቱን ስለምንሰማ እንድንወጣ አደረገ፣ አዎን ወንድማችንም ልክ እንደ እርሱ ነው። እናም በእንደዚህ አይነት አነጋገር ነበር ወንድሞቼ ያጉረመረሙትና በእኛ የተማረሩት።

፳፫ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ እንዲህ ስል ተናገርኳቸው—የእስራኤል ልጆች የነበሩት አባቶቻችን፣ የጌታን ቃላት ባይሰሙ ኖሮ ከግብፃውያን እጅ ይወጡ ነበር ብላችሁ ታምናላችሁን?

፳፬ አዎን፣ ጌታ ሙሴን እነርሱን ከባርነት እንዲያወጣቸው ባያዘው ኖሮ ከባርነት ይወጣሉ ብላችሁ ትገምቱ ነበርን?

፳፭ አሁን የእስራኤል ልጆች በባርነት እንደነበሩ ታውቃላችሁ፤ እናም ለመጽናት አስቸጋሪ የሆኑ ስራዎችን እንደተሸከሙ ታውቃላችሁ፤ ስለዚህ ከባርነት መውጣታቸው ለእነርሱ የሚያስፈልግ ጥሩ ነገር እንደነበርም ታውቃላችሁ።

፳፮ አሁን ሙሴ ያንን ታላቅ ስራ እንዲሰራ በጌታ መታዘዙን ታውቃላችሁ፤ እናም በእርሱ ቃል የቀይ ባህር ውሃ ወዲህና ወዲያ ተከፍሎ እንደነበርና፣ በደረቁ መሬት እንደተጓዙ ታውቃላችሁ።

፳፯ ነገር ግን የፈርዖን ወታደሮች የሆኑት ግብፃውያን በቀይ ባህር ውስጥ እንደሰጠሙ ታውቃላችሁ።

፳፰ እናም እነርሱ በምድረበዳ ውስጥ መና እንደበሉ ደግሞ ታውቃላችሁ።

፳፱ አዎን እናም ሙሴ በእርሱ ያለውን የእግዚአብሔር ኃይል በመጠቀም ቃል እንደተናገረ፣ ድንጋዩን እንደመታና የእስራኤል ልጆች ጥማታቸውን ማርካት እንዲችሉ ውሃን እንዳወጣላቸው ታውቃላችሁ።

እናም በጌታ አምላካቸው መድኃኒታቸው ቢመሩም፣ ከፊታቸው በመሄድ በቀን ቢመራቸውም፣ እናም በጨለማም ብርሃን ቢሰጣቸው፣ እናም ሰዎች እንዲቀበሉት አስፈላጊ የሆኑትን ሁሉንም መልካም ነገሮችን ቢሰራም ልባቸውን አጠጠሩበት፣ እንዲሁም አእምሮአቸውን አሳወሩ፣ እናም በሙሴ ላይ እንዲሁም በእውነተኛውና በህያው እግዚአብሔር ላይ ክፉ ተናገሩ።

፴፩ እናም እንዲህ ሆነ እንደቃሉ አጠፋቸው፤ እናም እንደቃሉ መራቸው፣ እናም እንደቃሉ ሁሉንም ነገሮች ለእነርሱ አደረገ፤ እናም እንደቃሉ ያልሆነን በስተቀር የተደረገ ምንም ነገር አልነበረም።

፴፪ እናም የዮርዳኖስን ወንዝ ካቋረጡ በኋላ በምድሪቱ ያሉትን ልጆች እንዲያስወጡ፣ አዎን፣ እነርሱን እንዲያጠፉአቸውና እንዲበትኑአቸው ብርቱ አደረጋቸው።

፴፫ እናም አሁን በአባቶቻችን እንዲወጡ የተደረጉት፣ በቃልኪዳኑ ምድር ውስጥ ይኖሩ የነበሩት የዚህ ምድር ልጆች፣ ፃድቃን ናቸው ብላችሁ ትገምታላችሁን? እነሆ እኔ አይደሉም እላችኋለሁ።

፴፬ እነርሱ ፃድቃን ቢሆኑ አባቶቻችን ከእነርሱ የበለጠ የተመረጡ ይሆናሉ ብላችሁ ታስባላችሁን? እኔ አይሆኑም እላችኋለሁ።

፴፭ እነሆ ጌታ ሁሉንም ሕዝብ በአንድ ዐይን ይመለከታል፤ ፃድቅ የሆነ በእግዚአብሔር የተወደደ ነው። ነገር ግን እነሆ እነዚህ ሕዝቦች የእግዚአብሔርን ማንኛውንም ቃል አልተቀበሉም፣ እናም እነርሱ ሙሉ በሙሉ በኃጢያት ጠውልገው ነበር፤ እናም የእግዚአብሔር የቁጣው ሙላት በእነርሱ ላይ ነበር፤ እናም ጌታ ምድሪቷን በእነርሱ ላይ ረገማት፣ እንዲሁም ለአባቶቻችን ባረካት፤ አዎን፣ እነርሱ ይጠፉ ዘንድ በእነርሱ ላይ ረገማት፣ እናም አባቶቻችን በእርሷ ላይ ኃይል ይኖራቸው ዘንድ ባረከላቸው።

፴፮ እነሆ ጌታ ሰዎች መኖር እንዲችሉባት ምድርን ፈጠረ፤ እናም ልጆቹ የእነርሱ ያደርጓት ዘንድ ፈጠራቸው።

፴፯ እናም ፃድቃን የሆኑትን ሀገሮች ያስነሳል፤ እናም ኃጢኣተኞች የሚኖሩባትን ሀገር አጠፋ።

፴፰ እናም ፃድቃንን በጣም አስፈላጊ ወደሆነው ምድር መራ፤ እናም ኃጢአተኞችን አጠፋቸው፣ እንዲሁም እነርሱ ባደረጓቸው ነገሮች ምድሪቱን ረገማት።

፴፱ በላይ በሰማይ ይገዛል፣ ምክንያቱም ሰማይ ዙፋኑ ነው፣ እናም ይህቺ ምድር መርገጫው ናት።

እናም አምላካቸው አድርገው የሚቀበሉትን ይወዳቸዋል። እነሆ እርሱ አባቶቻችንን ወደዳቸው፣ እናም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል፣ አዎን፣ ለአብርሃም፣ ለይስሀቅ፣ እና ለያዕቆብ እንኳን፤ እናም የገባቸውን ቃልኪዳኖች አስታወሰ፤ ስለዚህ እነርሱን ከግብፅ ምድር አወጣቸው።

፵፩ እናም ልክ እንደ እናንተ ልባቸውን ስላጠጠሩ፤ በምድረበዳ ውስጥ በበትሩ ቀጣቸው፤ እናም በክፋታቸው ምክንያት ጌታ ቀጣቸው። የሚበሩ መርዛምን እባብ በመካከላቸው ላከ፤ እናም ከተነደፉ በኋላም ይድኑ ዘንድ መንገዱን አዘጋጀ፤ እናም ማድረግ ያለባቸው ነገር መመልከት ብቻ ነበር፤ እናም በድርጊቱ ቀላልነት የተነሳ ብዙዎች የጠፉ ነበሩ።

፵፪ እናም እነርሱ በተለያዩ ጊዜያት ልባቸውን አጠጠሩ፣ እናም በሙሴ ላይ እንዲሁም ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ ክፉን ተናገሩ፤ ሆኖም ወደር በሌለው በእርሱ ኃይል ወደቃልኪዳኑ ምድር እንደተመሩ እናንተ ታውቃላችሁ።

፵፫ እናም አሁን ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች በኋላ ክፉ የሆኑበት ጊዜ መጣ፣ አዎን፣ እስኪጠወልጉም ድረስ፤ እናም እንደማስበው በዚህ ቀን ሊጠፉ የተቃረቡ ናቸው፣ ጥቂቶች በምርኮ ከሚወሰዱ በስተቀር እነርሱ የሚጠፉበት ቀን በእርግጥ እንደሚመጣ አውቃለሁ።

፵፬ ስለዚህ ጌታ አባቴን ወደ ምድረበዳው መሄድ እንዳለበት አዘዘው፤ እናም አይሁዶች ሊገድሉት ሞከሩ፤ አዎን እናንተም ደግሞ ልትገድሉት ሞከራችሁ፤ ስለዚህ እናንተ ህይወቱን ለማጥፋት ፈለጋችሁ፣ ስለሆነም እናንተ በልባችሁ ገዳዮች ናችሁ፣ እናም ልክ እንደ እነርሱ ናችሁ።

፵፭ እናንተ ክፉን ለማድረግ ፈጣን፣ ግን ጌታ አምላካችሁን ለማስታወስ የምትዘገዩ ናችሁ። መልአክን አይታችኋል፣ እናም ተናግሯችኋል፤ አዎን ድምፁንም በየጊዜው ሰምታችኋል፤ እናም በትንሽ ለስላሳ ድምፅ ተናግሯችኋል፣ ነገር ግን እናንተ ደንዝዛችኋል፣ ስለዚህ ቃሉ ሊሰማችሁ አልቻለም፤ ስለዚህ እርሱ ሲናገራችሁ ድምፁ ልክ መሬትን እንደምትሰነጠቅ አይነት እንድትናወጥ እንዳደረጋት ነጎድጓድ ነበር።

፵፮ እናም ደግሞ ጌታ ኃያል በሆነው ቃሉ ኃይል መሬት ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትኖር ማድረግ እንደሚችል ታውቃላችሁ፤ አዎን እናም በቃሉ ጠማማውን ማቃናት እንደሚችል ታውቃላችሁ፣ እናም የተቃናው ቦታ ይሰበራል። አቤቱ፣ ለምን እናንተ በልባችሁ ደንዳኖች ትሆናላችሁ?

፵፯ እነሆ በእናንተ ምክንያት ነፍሴ ተጨነቀች፣ እንዲሁም ልቤ ቆስሏል፤ ለዘለዓለም እናንተ እንዳትጣሉ እፈራለሁ። እነሆ በእግዚአብሔር መንፈስ በመሞላቴ ሰውነቴም ጥንካሬ የለውም።

፵፰ እናም አሁን እንዲህ ሆነ እነዚህን ቃላት ስናገር እነርሱ በእኔ ተቆጥተው ነበር፣ እና ወደባህር ጥልቅ ሊወረውሩኝ ፈለጉ፤ እናም ሊይዙኝ ወደእኔ ሲመጡ እንዲህ በማለት ተናገርኳቸው—ሁሉን በሚገዛው በእግዚአብሔር ስም እንዳትነኩኝ አዛችኋለሁ፣ ስጋዬ እስከሚበላ ድረስ በእግዚአብሔር ኃይል ተሞልቻለሁና፤ እና ማንኛውም እጁን በላዬ ላይ ያደረገ እንደደረቀ ሸንበቆ ይኮማተራል፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ኃይል ፊት እንደከንቱ ነገር ይሆናል፣ እግዚአብሔር ይቀጣዋልና።

፵፱ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ፣ በአባታቸው ላይ ከእንግዲህ ማጉረምረም እንደሌለባቸው፣ ከእኔ ጋር ለመስራት መቃወም እንደሌለባቸው ተናገርኳቸው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር መርከብ እንድሰራ አዞኛልና።

እናም እንዲህ አልኳቸው—እግዚአብሔር ሁሉንም ነገሮች እንድሰራ ካዘዘኝ፣ መስራት እችላለሁ። እርሱ ይህንን ውሃ ወደ ምድር ተለወጥ እንድለው ካዘዘኝ ውሃውም ምድር ይሆናል፤ እናም ይህንንም ካልኩት እንዳዘዝኩት ይሆናል።

፶፩ እናም አሁን ጌታ ይህን ያህል ታላቅ ኃይል ካለው፣ እንዲሁም በሰዎች ልጆች መካከል ብዙ ተዓምራትን ካደረገ፣ እኔም መርከቡን መስራት እንድችል ማስተማር እንዴት አይቻለውም?

፶፪ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ ለወንድሞቼ ብዙ ነገሮችን ስለተናገርኳቸው ዝም አሉ፣ እናም ከእኔ ጋር መከራከር አልቻሉም፤ ለብዙ ቀናትም እጃቸውን በእኔ ላይ መጫንም ሆነ በጣቶቻቸው ሊነኩኝ አልደፈሩም። አሁን፣ የእግዚአብሔር መንፈስ እጅግ ኃይለኛ ስለነበረ፣ ይህን ለማድረግ ያልደፈሩትም፣ በእኔ ፊት እንዳይኮማተሩ ፈርተው ነው፤ እናም እንደዚህም በእነርሱ ላይ ተፅዕኖ ነበረው።

፶፫ እናም እንዲህ ሆነ፣ ጌታ እንዲህ አለኝ—በወንድሞችህ ላይ እንደገና እጅህን ዘርጋ እናም እነርሱ በአንተ ፊት አይኮማተሩም፣ ነገር ግን አንቀጠቅጣቸዋለሁ፣ እናም ይህንን የማደርገው አለ ጌታ፣ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቁ ዘንድ ነው።

፶፬ እናም እንዲህ ሆነ፣ በወንድሞቼ ላይ እጄን ዘረጋሁ፣ እናም እነርሱ አልተኮማተሩም ነበር፤ ነገር ግን ጌታ ልክ እንደተናገረው አንቀጠቀጣቸው።

፶፭ እናም ከዚያ ጌታ ከአንተ ጋር መሆኑን በእርግጥ እናውቃለን፣ የጌታ ኃይልም እኛን እንዳንቀጠቀጠን እናውቃለንና አሉ። እናም በፊቴ ወደቁ፣ እና እኔን ለማምለክ ሞክሩ፣ ነገር ግን እኔን እንዲያመልኩ አልፈቀድኩላቸውም፣ እንዲህም አልኩ—እኔ ወንድማችሁ ነኝ፣ አዎን፣ ታናሽ ወንድማችሁ፤ ስለዚህ ጌታ አምላካችሁን አምልኩ፣ እናም አባትና እናታችሁን አክብሩ፣ ጌታ አምላካችሁ በሚሰጣችሁ ምድር እድሜያችሁ እንዲረዝም።